የማኅበራዊ ሣይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ የምርምር ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ከዩኒቨርሲቲው የምርምር ዳይሬክቶሬት ጋር በመተባበር ለማኅበራዊ ሣይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ እንዲሁም ለስነ-ትምህርትና ስነ-ባህርይ ሣይንስ 32 መ/ራን ከመጋቢት 2-6/2011 ዓ/ም ለተከታታይ 5 ቀናት በጥናትና ምርምር አተገባበር ላይ ያተኮረ ስልጠና ሰጥቷል፡፡ ምስሎቹን ለመመልከት ከዚህ ይጫኑ

የማኅበራዊ ሣይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ የምርምር ማስተባበሪያ ጽ/ቤት አስተባባሪ ዶ/ር እንዳልካቸው ኃይሉ እንደገለፁት ስልጠናው የመ/ራንን የምርምር ክሂሎት በማጎልበት የተሻለ ጥራትና መጠን ያላቸው ጥናትና ምርምሮች እንዲከናወኑና መምህራን በምርምር ትግበራው ላይ ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ይረዳል፡፡ በተጨማሪም ፕሮፖዛሎች እንዲቀርቡ ጥሪ ሲደረግ የምርምር ፕሮፖዛል በማስገባት በተሻለ ሁኔታ እንዲሳተፉና ስልጠናውን ተጠቅመው በአጭር ጊዜ ውስጥ የያዙትን ጥናትና ምርምር እንዲያጠናቅቁም አስተባባሪው አሳስበዋል፡፡

ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የመጡት ዶ/ር ሙሉጌታ ተካ መጠናዊ /Quantitative/ እና አይነታዊ /Qualitative/ ምርምር እንዲሁም SPSS/ Statistical package for social science/ ሶፍትዌር አጠቃቀም ላይ ያተኮረ ስልጠና ሰጥተዋል፡፡

መጠናዊ /Quantitative/ ምርምር መላምትን ወይም ቲዮሪን ተመርኩዞ የሚካሄድ፣ መጠንን ገላጭ የሆነና የመረጃዎቹ አይነት በቁጥር የሚገለፁ ሲሆን በስታትስቲካዊ ዘዴ የሚተነተኑ መሆኑን ዶ/ር ሙሉጌታ ገልፀዋል፡፡ በመጠናዊ ምርምር መረጃዎችን ወደ ቁጥር መቀየር፣ ቲዮሪ ቴስት ማድረግ፣ የተገኘውን መረጃ ዝምድና ለማሳየት ስታትስቲካዊ ቴስት መጠቀም የመሳሰሉ ጉዳዮች በስፋት ተቃኝተዋል፡፡

አይነታዊ /Qualitative/ ምርምር መረጃዎችን በአሃዝ የሚገልፅና በትረካ ወይም በገለፃ መልክ የሚቀርብ መሆኑን አሠልጣኙ ተናግረዋል፡፡ በሌላ በኩል SPSS በጣም ሰፊና የተደራጀ እውቀት የሚገኝበት ሶፍትዌር ሲሆን መረጃዎችን በቀላሉ ለመተንተን የሚረዳ ነው ብለዋል፡፡
በስልጠናው ሂደት የተለያዩ የቡድን ውይይቶችና ተግባራዊ ልምምዶች የተካሄዱ ሲሆን በርካታ ጥያቄዎችም ተነስተው ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

ሰልጣኝ መ/ራን በሰጡት አስተያየት ስልጠናው አጓጊና ሳቢ ከመሆኑም በላይ ትልቅ ትምህርት ያገኙበትና መሰረታዊ ቁም ነገሮችን የጨበጡበት መሆኑን ገልፀው ስልጠናው ቀጣይነት ቢኖረው መልካም ነው ብለዋል፡፡

የማኅበራዊ ሣይንስና ስነ ሰብ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ሙሉጌታ ደበሌ በፕሮግራሙ ማጠቃለያ ላይ እንደገለፁት መ/ራን ከስልጠናው ያገኙትን እውቀት መሰረት በማድረግ የነበረውን ተነሳሽነት ማጠናከርና በተለያዩ የምርምር ተግባራት ላይ መሳተፍ እንደሚጠበቅባቸው ጠቁመዋል፡፡ በቀጣይም ኮሌጁ የተለያዩ ተመሳሳይ ስልጠናዎችን እንደሚያዘጋጅም ተናግረዋል፡፡