በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ108ኛና በሀገር አቀፍ ለ43ኛ ጊዜ የሚከበረው ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን /ማርች 8/ ‹‹በላቀ ትኩረትና ቁርጠኝነት ለሴቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት!›› በሚል መሪ ቃል መጋቢት 9/2011 ዓ/ም በዩኒቨርሲቲው ተከብሯል፡፡ ምስሎቹን ለመመልከት ከዚህ ይጫኑ

የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸውን ያስተላለፉት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በመክፈቻ ንግግራቸው አለም አቀፍ የሴቶች ቀን እንዲከበር ሲወሰን ሴቶች የሚደርስባቸውን መድሎ በቅንጅት በጋራ ታግሎ ለመቀነስ ወይም ለማስወገድ ቃል የሚገባበት መድረክ እንዲሆን ታስቦ መሆኑን ገልፀዋል፡፡  ከዚህ ጋር ተያይዞ የሴቶች እኩልነት ተከብሮ በልማት ተሳታፊ በመሆን ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ሁኔታ ለማረጋገጥ በሀገርና በዩኒቨርሲቲውም ደረጃ የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን  ተናግረዋል፡፡ በትምህርት ረገድ በተለይም በ1ኛ እና 2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች የሴቶች ተሳትፎ በእጅጉ እየተሻሻለ የመጣ ሲሆን በዩኒቨርሲቲ ደረጃም ተማሪዎች ጥሩ ውጤት እያመጡ ናቸው ብለዋል፡፡ በአጠቃላይ  በሁሉም ሴክተሮች የፆታ እኩልነት እየተሻሻለ መምጣቱን ፕሬዝደንቱ ተናግረዋል፡፡

የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሪት ሰናይት ሳህሌ እንደተናገሩት በዓሉ ሴቶችን ካለመቻል ወደ መቻል ለማምጣት ሳይሆን በተለያዩ ተፅዕኖዎች ወደ ኋላ የቀሩ ሴቶችን  ከተፅዕኖዎች  በመታደግ  ተፈጥሯዊ የሆነ ብቃታቸውን ለመጠበቅ መነሳሳትን የሚያመላክት ነው፡፡  ‹‹ከእያንዳንዱ ወንድ ጀርባ ጠንካራ ሴት አለች›› የሚለው አባባል ብዙ የሚያስተምረን ሲሆን ሴቶችን መደገፍና  ማሳተፍ እንቅስቃሴ የመሰልጠንና የዘመናዊነት ምልክት መሆኑን ማሳያ ከመሆኑም በላይ የወንዱ ጥንካሬ መሰረት ሴቷ መሆኗን የሚያመላክት ነው ብለዋል፡፡  እንደ ዳይሬክተሯ ገለፃ የሴቷ ጥንካሬ ለወንዱ ሚና ቀላል አለመሆኑ ሊስተዋል ይገባል፡፡

ዳይሬክተሯ አክለውም እየተከበረ ያለው የሴቶች ቀን በአገራችን የመጣውን ለውጥ ተከትሎ በጣም በአስተውሎትና በቆራጥነት ሊሰሩ የሚገባቸው ወሳኝ የሆኑ መዋቅሮች ላይ ለዘመናት ታምና ለመምራትና ልትሾም ይቅርና በቀደሙት ጊዜያት ሰለጠኑ በሚባሉት ሀገራት እንኳን የሚመራትን  መንግስት መምረጥ መብት ያልነበራት ይህች ሴት  በአሁኑ ወቅት አገርን እንድትመራ መደረጉ ትልቅ ለውጥ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡  ዩኒቨርሲቲውም ይህንን ልምድ በመቅሰም ሴቶችን ከከፍተኛ አመራር አንስቶ በየደረጃው ባሉ የአመራርነት  ቦታዎች ላይ ለማብቃት ተግቶ በመስራት ላይ የሚገኝ ቢሆንም አሁንም በስርዓተ ፆታ ምጥጥን ላይ ያለውን ክፍተቶች በማጤን ባሉት ሁሉም ቦታዎች ላይ እኩል ተሳታፊ እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታ እንዲፈጥርም ጠይቀዋል፡፡ በመጨረሻም እኛ ሴት ሰራተኞች ለዘመናት የተጫነብንን ሴት ጎታች የባህል ተፅዕኖ ወደ ኋላ በመተው ሳንዳከም ተምሳሌት የሚሆኑ ጠንካራ ሴቶችን ልምድ በመቅሰምና ጥንካሬያችንን አሟጠን በመጠቀም ለአገርና ለትውልድ የሚጠቅም አንዲት ጠብታ ለመጨመር በንቃት ልንተጋ ይገባል ሲሉም አሳስበዋል፡፡

የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ዳይሬክቶሬት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ መሰለ መርጊያ ባቀረቡት ሰነድ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ሴቶች በፆታቸው የሚደርስባቸውን መድሎና ጭቆና ለማስቀረትና ለማስወገድ  ካደረጉት ትግል ጋር ተያይዞ  የሚከበር ሲሆን የቀኑ መከበር  ምክንያት በአስራ ዘጠነኛው  ክፍለ ዘመን መጀመሪያ በአውሮፓና ቀጥሎም በአሜሪካ የተስፋፋው የኢንደስትሪ  ዘርፍ መስፋፋት መሆኑን ያስረዳል፡፡  በወቅቱ በኢንደስትሪዎች ውስጥ ይሰሩ የነበሩ ሴቶች ፆታን  መሰረት ያደረጉ መድሎዎች ይደርሱባቸው እንደነበርና በወቅቱ ሴቶች በዘርፉ ከወንዶች እኩል ተሳትፎ የነበራቸው ቢሆንም ተገቢውን ክብርና ዕውቅና እንዲሁም የሚገባቸውን ጥቅምም እንደማያገኙ ሰነዱ ጠቁሟል፡፡

በወቅቱ የነበሩ ሴቶች ሲደርስባቸው የነበረውን መድልዎና ጭቆና በመቃወም የከረሩ ጥያቄዎችን በማንሳትና ከፍተኛ ንቅናቄዎችን በመፍጠር ድምፃቸውን በማሰማት በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሴቶች እኩልነትና መብት መከበር ከሚንቀሳቀሱ ሰዎች ዘንድ ድጋፍ ካገኙበት ጊዜ ጀምሮ አለም አቀፍ የሴቶች ቀን ከፆታ መድሎዎች ለመላቀቅ ከተደረገው ትግል ጋር በእጅጉ ተቆራኝቶ ሴቶች በፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ከወንዶች እኩል ተሳታፊ የሚሆኑበትን ምቹ ሁኔታ ለማረጋገጥ ሁሉም ዜጋ የበኩሉን ድርሻ እንዲያበረክት ግንዛቤ ለመፍጠር በሚያስችል መልኩ ይከበራል፡፡

በቀረበው ሰነድ መነሻነት በተካሄደው ውይይት ሴቶችን ወደ ከፍተኛ አመራሪነት ለማምጣት፣ ሴቶችን በምርምር እንዲሳተፉ ለማብቃት፣ የአሰተዳደር ዘርፍ ሴት ሠራተኞችም በምርምር እንዲሳተፉ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት ንዲሁም ለሴት ተማሪዎች የዲፓርትመንት ምርጫ፣ የቲቶሪያ ዝግጅትና  መጠነ ማቋረጥን ለመቀነስ የሚሠሩ ተግባራት በትኩረት ሊሠሩ እንደሚገባ ተጠቅሷል፡፡

በፕሮግራሙ የሴቶችን የፆታ እኩልነት ትግል ዙሪያ አበረታችና አነቃቂ የሆኑ የሥነ-ፅሑፍ ሥራዎች የቀረቡ ሲሆን ዩኒቨርሲቲውን ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ጨምሮ ከተለያዩ የሥራ ክፍሎች የተወጣጡ ሴት መምህራን፣ የአስተዳደር ዘርፍ ሠራተኞችና ሴት ተማሪዎች ታድመዋል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት