በ2011 የትምህርት ዘመን 1ኛ መንፈቅ ዓመት የላቀ ውጤት ያስመዘገቡ የቴክኖሎጂና የውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩቶች ሴት ተማሪዎች መጋቢት 12/2011 ዓ.ም የማበረታቻ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በመክፈቻ ንግግራቸው ከፍተኛ ውጤት ያመጡ ሴት ተማሪዎችን መሸለም የበለጠ እንዲሠሩ የሚያደርግና ለሌሎች ተማሪዎችም መነቃቃትን የሚፈጥር ነው ብለዋል፡፡ ምስሎቹን ለመመልከት ከዚህ ይጫኑ

የዕለቱ የክብር ዕንግዳ አምባሳደር ገነት ዘውዴ በትምህርት ዓለም፣ በሚኒስቴርነትና በአምባሳደርነት የሥራ ዘመን እንዲሁም በማኅበራዊ ህይወታቸው ያሳለፉትን ተሞክሮ ለተማሪዎች አጋርተዋል፡፡ ሴቶች በግለሰባዊም ሆነ በማኅበራዊ ህይወታቸው የተለያዩ ተግዳሮቶች ያሉባቸው መሆኑን የተናገሩት አምባሳደሯ ነገር ግን ጫናውን ተቋቁመው ከፍተኛ ደረጃ የደረሱ ሴቶችን አብነት በማድረግ ሴት ተማሪዎች ከወዲሁ ብርታትን መሰነቅ ይገባችኋል ብለዋል፡፡

አምባሳደር ገነት በአሁኑ ሰዓት ከቀደመው ጊዜ በተሻለ ሴት ተማሪዎች በሣይንስና ቴክኖሎጂ የትምህርት ዘርፎች ያላቸው ተሳትፎ በእጅጉ ማደጉን ተናግረው በሥራው ዓለምም ስኬታማ ለመሆን ሴቶች በራስ መተማመናቸውን ማሳደግና ሙሉ አቅማቸውን መጠቀም እንዳለባቸው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የሽልማት ፕሮግራሙ ለአዲስ ገቢ ሴት ተማሪዎች ጠቃሚ መልዕክቶችን ለማስተላለፍና ከነባር ተማሪዎች ልምድ እንዲቀስሙ ለማድረግ በዓመቱ መጀመሪያ የሚከናወን እንደነበር የጠቀሱት የቴክኖሎጂና የውኃ ቴክኖሎጂ ኢንቲትዩቶች የሥርዓተ ፆታ ጉዳዮች አስተባባሪ ወ/ሪት አዳነች እልፍነህ በገጠሟቸው የአሠራር ችግሮች የዘንድሮው ፕሮግራም ከታቀደለት ጊዜ መዘግየቱን ተናግረዋል፡፡

በፕሮግራሙ ከ3.88 – 4፡00 ነጥብ ያመጡ 13 ከ2ኛ እስከ 4ኛ ዓመት ተማሪዎች ሽልማት የተበረከተላቸው ሲሆን ከተሸላሚዎቹ ሦስቱ 4 ነጥብ ያመጡ ናቸው፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት