በምርምር ዳይሬክቶሬት አዘጋጅነት ዓመታዊ የምርምር ዓውደ ጥናት (Annual Research Review Workshop) የዘርፉ ባለሙያዎች በተገኙበት መጋቢት 06/2011 ዓ.ም ተካሂዷል፡፡
በዕለቱ 5 የምርምር ጽሑፎች የቀረቡ ሲሆን በዩኒቨርሲቲው ትምህርታቸውን አጠናቀው በሥራ ዓለም ያሉ ተማሪዎች ውጤታማነት፣ የመሬት አጠቃቀምና አያያዝ ለውጥ በአፈር መሸርሸር ላይ ያመጣው ተፅዕኖ፣

የHIV/AIDS በሽታ መስፋፋት በጋሞ ጎፋ ዞን፣ የነጭ ሳር ብሄራዊ ፓርክ የስነ-ምህዳር ይዞታ እና በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የእንግሊዝኛ ቋንቋ ተግባቦትና አጠቃቀም ችግሮች ላይ ያተኮሩ ናቸው፡፡ ምስሎቹን ለመመልከት ከዚህ ይጫኑ

የምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተሾመ ይርጉ ዓውደ ጥናቱ እየተካሄዱ ያሉ ምርምሮችን ክፍተት በመለየት የደረሱበትን ደረጃ መገምገም፣ የተጠናቀቁ ምርምሮችን ጥራትና ችግር ፈቺነት መመዘን እንዲሁም ምርምሮቹ ሳይንሳዊ መሆናቸውን ተመራማሪዎችና የዘርፉ ባለሙያዎች ሀሳብ እንዲሰጡበትና ልምዳቸውን እንዲያጋሩ ለማድረግ ያለመ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በተመሳሳይ በየኮሌጆቹ በሚገኙ 16 የምርምር ማስተባበሪያ ቢሮዎች አማካይነት 269 የሚሆኑ የምርምር ሥራዎች የደረሱበትን ሂደት ማቅረባቸውን ዶ/ር ተሾመ አክለዋል፡፡

በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚደረጉ ምርምሮች የኅብረተሰቡን እድገትና ኑሮ ለማሻሻል ከፍተኛ ድርሻ ስላላቸው አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲም ለምርምሮችና ዩኒቨርሲቲውን መምህራን እውቀት በምርምር ለማሳደግ ትኩረት በመስጠት እየሠራ ይገኛል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ እንደተናገሩት የምርምር ዋና ዓላማ ጥናት ማካሄድ ብቻ ሳይሆን የምርምር ግኝትና ውጤት ወደ መሬት ወርዶ የማህበረሰቡን ዘርፈ ብዙ ችግሮችን እንዲፈታ እንዲሁም ለሳይንሱ ዕድገት አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ማድረግ በመሆኑ በአሁኑ ወቅት ዩኒቨርሲቲያችን የምርምር ዘርፉን አቅም ለማጎልበትና ለማስፋፋት የመምህራንን አቅም የማጎልበት፣ የድህረ-ምረቃ ፕሮግራሞችን የማስፋፋት፣ የምርምር ማዕከላትን ከአስፈላጊ ግብዓቶች ጋር የማሟላት ተግባራት ላይ ትኩረት ሰጥቶ  እየሠራ ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር ዩኒቨርሲቲው የተለያዩ ችግር ፈቺ የምርምር ሥራዎችን በዓለም አቀፍ ጆርናሎች ላይም እያሳተመ እንደሚገኝ ፕሬዝደንቱ ጠቁመዋል፡፡

በዓውደ ጥናቱ ያላለቁ ምርምሮችም ቀርበው ለቀጣይ መስተካከል ያለባቸው ጉዳዮች ተጠቁመው ዳብረው እንዲቀርቡ አስፈላጊው ሁሉ ድጋፍ የሚደረግ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
በዓውደ ጥናቱ የዩኒቨርሲቲው የሥራ ኃላፊዎችና መምህራን ተገኝተዋል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት