የዩኒቨርሲቲው ኮሚዩኒቲ ት/ቤቶች የ2011 የትምህርት ዘመን የ1ኛ ሴሚስተር የወላጅ ቀን በዓልን የካቲት 30/2011 ዓ.ም በድምቀት አክብረዋል፡፡

በሁሉም የትምህርት ዕርከኖች በሴሚስተሩ የተማሪዎች ሥነ-ምግባርና የባህርይ ለውጥ በታቀደው መሠረት ግብ መምታቱን ለመፈተሽ፣ የተማሪው ውጤት ከታለመው ዒላማ ምን ያህል እንደተሳካ ለመገምገም እንዲሁም ለተማሪው ባህርይና ውጤት የወላጅና የመምህራን ድጋፍና ክትትል ያለው ፋይዳ ላይ ለመምከር የወላጅ ቀን በዓል ተዘጋጅቷል፡፡ ምስሎቹን ለመመልከት ከዚህ ይጫኑ

የማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ እንደገለፁት አብዛኛዎቹ ተማሪዎች በሴሚስተሩ መካከለኛ አፈፃፀም ያስመዘገቡ ሲሆን ከፍተኛ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች ቁጥር አነስተኛ ነው፡፡ በቀጣይ ሴሚስተር ይህንን ለማሻሻል ከመምህራንና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ለመሥራት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ተነጋግረው መግባባት ላይ መድረሳቸውን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

የኮሚዩኒቲ 2ኛ ደረጃና መሰናዶ ት/ቤት ር/መምህር አቶ ካምቦ ከተማ ባቀረቡት ሪፖርት እንደተገለጸው ከተማሪዎች ሥነ-ምግባር አኳያ በደንብ ልብስ፣ በፀጉር አቆራረጥ፣ በውበት ቀለሞች አጠቃቀም እና በተንቀሳቃሽ ስልክ አጠቃቀም መሻሻል ታይቷል፡፡ ት/ቤቱ ሳያውቅ ለተከታታይ ከ3-4 ቀን የቀሩ ተማሪዎች በክፍል ኃላፊ መምህር አማካይነት በወላጅ እንዲመከሩ በመደረጉ ከቀድሞው በተሻለ በትምህርት ገበታ ላይ መገኘት ችለዋል፡፡ የፈተና ሥርዓቱ ከኩረጃ እንዲፀዳም በክፍል በስብጥር እንዲፈተኑና እያንዳንዱ ተማሪ ራሱን ችሎ በግል እንዲሠራ ተደርጓል፡፡

ሰዓት ማርፈድ፣ የመማር ፍላጎት ማነስ፣ የትምህርት ግብዓቶችን አሟልቶ አለመምጣት እና የትምህርት ውጤታቸውን ለወላጅ ለማሳየት ፈቃደኛ አለመሆን በተማሪዎች በኩል እንዲሻሻሉ የተቀመጡ ነጥቦች ናቸው፡፡
የተማሪዎችን የደንብ ልብስ፣ የፀጉር አሠራርና አቆራረጥ አለመቆጣጠር፣ ሰዓት ሲያረፍዱና በየዕለቱ የተማሩትን አለመከታተል፣ ምሳ አለማሰር እና የትምህርት ክፍያን በወቅቱ አለማጠናቀቅ በወላጆች በኩል የሚታዩ ክፍተቶች መሆናቸው ተገልጿል፡፡

ወላጆች በሰጡት አስተያየት የመማሪያ መጽሐፍት እጥረት፣ የትምህርት ቤት ክፍያ ሁኔታ ምቹ አለመሆን እና የሰርቪስ አሰጣጥ ችግሮችን ጠቅሰው ትምህርት ቤቱን ሞዴል ከማድረግ አንፃር እና ዝቅተኛ ውጤት ያመጡ ተማሪዎችን ለማሻሻል በቀጣይ ስለሚከናወኑ ሥራዎች ጥያቄዎችን አንስተው ከመድረኩ ምላሽ ተሰጥቷቸዋል፡፡

በበዓሉ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ ተማሪዎችና የተማሪ ወላጆች ተገኝተዋል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት