የICT ኢንኩቤሽን ስልጠና ተሰጠ

ዩኒቨርሲቲው ከደ/ብ/ብ/ሕ/ክ መንግሥት መገናኛና ኢንፎርሜሽን ኤጀንሲ ጋር በመተባበር ለመመረቅ 2 ዓመት ለቀራቸው 32 የሶፍትዌር ኢንጂነሪንግ፣ የኤሌክትሪካልና ኮምፒዩተር ኢንጂነሪንግ፣ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እና የኮምፒዩተር ሣይንስ ተማሪዎች በጥገና፣ በኔትዎርኪንግ እና በሶፍትዌር ዙሪያ ከመጋቢት 16-22/2011 ዓ/ም በኢንኩቤሽን ማዕከል ስልጠና ሰጥቷል፡፡ምስሉን ለማየት ከዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ቶሌራ ሴዳ እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው ለኢንደስትሪዎች ውጤታማነት የሚያግዝ እውቀትና ክሂሎት በማምረት እና በማሸጋገር የኢንደስትሪውንና የማኅበረሰቡን ችግር ይፈታል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ከኢንደስትሪዎች ጋር ትስስር መፍጠሩ የኢንደስትሪ ውጤቶች ጥራታቸውን የጠበቁና ለማኅበረሰቡ ፍላጎት ምላሽ የሚሰጡ እንዲሆኑ ያስችላል ያሉት ዶ/ር ቶሌራ ዩኒቨርሲቲው ከኢንደስትሪዎች ጋር የተሻለ ትስስር በመፍጠር የሥራ ፈጠራ ክሂሎት ያዳበሩ ዜጎችን በማፍራትና የማኅበረሰቡን መሠረታዊ ችግሮች በመለየት ለቴክኖሎጂ ሽግግር እንደሚሠራ ገልፀዋል፡፡

የቴክኖሎጂ ሽግግርና ኢንደስትሪ ትስስር የአዕምሯዊ ንብረት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ወንድማገኝ ጌታቸው እንደገለፁት የስልጠናው ዓላማ ተማሪዎች በንድፈ ሃሣብ የሚማሩትን የሚደግፍ የተግባር ክሂሎት በማስጨበጥ ከሥራ ጠባቂነት ተላቀው ሥራ በመፍጠር ገቢያቸውን የሚያሳድጉበትን መንገድ  እንዲያመቻቹ  አቅምን ማጎልበት ነው፡፡ በተጨማሪም ተማሪዎች ከመደበኛ ትምህርት ጎን ለጎን በኢንኩቤሽን ማዕከል የቴክኖሎጂ የተግባር ልምምድ ከማድረጋቸው ባሻገር  በተለያዩ የግንባታ እና መሰል ፕሮጀክቶች በመሳተፍ የፈጠራ እውቀት እንዲቀስሙ ዩኒቨርሲቲው የበኩሉን እየተወጣ ይገኛል ብለዋል፡፡

ስልጠናው በትምህርት መጀመሪያ ወቅት ቢሰጥ ይበልጥ ውጤታማ ይሆን ነበር ያለው የ4ኛ ዓመት የኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ ተማሪ ብስራት ታምራት በቀጣይም ዩኒቨርሲቲው የተማሪዎችን የሥራ ጠባቂነት አስተሳሰብ በመቀየር የሥራ ፈጠራ ባህልን ሊያዳብሩ የሚችሉ መሰል ሥልጠናዎችን ሊያመቻች ይገባል ብሏል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ከኤጀንሲው ጋር በመተባበር መሰል ሥልጠናዎችን ለመስጠት የውሉ ውጤታማነት እየታየ የሚታደስ የ5 ዓመት ስምምነት ያለው ሲሆን ሥልጠናዎችን ከመስጠት ባሻገር ሰልጣኝ ተማሪዎች መደበኛ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ የግል ሥራቸውን ለመፍጠርና ለማንቀሳቀስ በሚያመቻቸው መልኩ ኤጀንሲው ከደቡብ ንግድና ኢንደስትሪ ቢሮ ጋር ጥምረት በመፍጠር አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል፡፡