የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብ ለጌዴኦ ተፈናቃዮች የምግብ እህልና አልባሳት ድጋፍ አደረገ

በማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት አስተባባሪነት ‹‹አንድ ቅዳሜን ለሕዝቤ›› በሚል ወርሃዊ ፕሮግራም የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ከምዕራብ ጉጂ ዞን ለተፈናቀሉ የጌዴኦ ተፈናቃዮች ከግማሽ ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጣ የአልባሳትና የምግብ ዱቄት ድጋፍ አድርጓል፡፡ ከዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ የተወጣጣ ቡድንም ተፈናቃዮቹ ከሚገኙባቸው የመጠለያ ካምፖች መካከል አንዱ በሆነው ይርጋ ጨፌ መጠለያ ካምፕ መጋቢት 29/2011 ዓ/ም በመገኘት ጉብኝት አድርጓል፡፡ ምስሎቹን ለመመልከት ከዚህ ይጫኑ

የማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ ዩኒቨርሲቲው ‹‹አንድ ቅዳሜን ለሕዝቤ›› በሚል መሪ ቃል በየወሩ የበጎ አድራጎት ሲሠራ መቆየቱን አስታውሰው ይህም የበጎ አድራጎት ሥራ የመጋቢት ወር መርሃ-ግብር መሆኑን ገልፀዋል፡፡ እንደ ዶ/ር ተክሉ ማብራሪያ በዚህ የድጋፍ ማሰባሰብ ሂደት ላይ በሁሉም ካምፓሶች የሚገኙ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች፣ መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች የተሳተፉ ሲሆን ተማሪዎች የሦስት ቀን የስጋ ፕሮግራምን ወደ ሽሮ በመቀየር 482,859.60 ብር እንዲሁም የዩኒቨርሲቲው ሠራተኞች ከደመወዛቸው ከ129 ሺ ብር በላይ ማበርከታቸውን ገልፀዋል፡፡

ጥሬ ገንዘብ ከመስጠት የምግብ እህል መስጠቱ የተሻለ ሆኖ በመገኘቱ 260 ኩንታል የስንዴ ዱቄትና ከተማሪዎች፣ መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች የተሰበሰቡ 68 ማዳበሪያ አልባሳት ዕርዳታ የተበረከተ ሲሆን የተደረገው ድጋፍ በገንዘብ ሲተመን ከሰባት መቶ ሺ ብር በላይ መሆኑንም ዶ/ር ተክሉ ተናግረዋል፡፡

የልዑካን ቡድኑን በመምራት በስፍራው የተገኙት የፕሬዝደንት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ገዝሙ ቀልቦ ተፈናቃዮቹ ያሉበት ሁኔታ ልብ የሚነካና አሳዛኝ መሆኑን ገልፀው መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ከጎናቸው ሊቆም ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡ ሌሎች በአገሪቱ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎችና ተቋማትም ተመሳሳይ ድጋፍ ማድረግና ችግሩ በዘላቂነት እንዲፈታና መንግሥት ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው ተመልሰው የሚኖሩበትን ሁኔታ ለማመቻቸት የሚያደርገውን ጥረት ለማሳካት ሁላችንም በቅንነት ትብብር ማድረግ ይጠበቅብናል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የይርጋ ጨፌ ከተማ ከንቲባ ተወካይና የከተማው ደ/ኢ/ህ/ዴ/ን/ን/ቅ/ጽ/ቤት  ኃላፊ አቶ አበባየሁ ኢሳያስ በበኩላቸው የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብ ለተፈናቃዮች ላደረጉት ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበው ተፈናቃዮቹ አሁን ያሉበት ሁኔታ አጅግ በጣም አሳሳቢ በመሆኑ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የዕርዳታ እጁን እንዲዘረጋላቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ተፈናቃዮቹን ወደ ቀያቸው ለመመለስ የሚደረገው ጥረት ከሁለቱ ዞኖች አቅም በላይ በመሆኑ የደ/ብ/ብ/ህ እና ኦሮሚያ ክልሎች ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመቀናጀት እየሠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ከተፈናቃዮች መካከል በምዕራብ ጉጂ ዞን ተርጫ ወረዳ ዳሊሳ ዲቢሳ ቀበሌ ነዋሪ የነበሩት የ50 ዓመቱ አቶ ግርማ ጎዳና በዚሁ ቦታ ተወልደው ማደጋቸውን ገልፀው ከ2010 ጀምሮ እሳቸውና ቤተሰባቸው ተወልደው ካዳጉበትና ቤተሰብ ካፈሩበት ቀዬ ተፈናቅለው በችግር ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ለተፈናቃዮች እየተደረገ ያለው ዕርዳታ በቂ አለመሆኑን የጠቆሙት አቶ ግርማ መንግስት የሕግ የበላይነትን በማስከበር ወደ ቀያችን ሊመልሰን ይገባል ብለዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ማኀረበረሰብ ላደረገላቸው ድጋፍ ምስጋና በማቅረብ ንግግራቸውን የጀመሩት ሌላዋ ተፈናቃይ ወ/ሮ አበራሽ ዎቴ የሚኖሩበት መጠለያ በራሳቸው ጉልበት በቅጠላ ቅጠል የተሠራ በመሆኑ ከምግብና ከአልባሳት ችግሩ በተጨማሪ ተፈናቃዩ ፀሐይና ዝናብ እየተፈራረቀበት ለበሽታ እየተዳረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ስለሆነም የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ከምንጊዜውም በላይ ከጎናቸው እንዲቆሙላቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ከልዑካን ቡድኑ አባላት መካከል የዩኒቨርሲቲው በጎ አድራጎት ክበብ ተጠሪ ተማሪ መሃሪ ዳርሰማ  በዚህ በሰለጠነና ዓለም አንድ መንደር እየሆነች ባለችበት ወቅት ኢትዮጵያውያን ከገዛ አገራቸውና መሬታቸው ተፈናቅለው በረሃብ፣ በበሽታ፣ በፀሐይና ዝናብ ሲንገላቱ ማየት እጅግ ልብ የሚነካና አሳዛኝ መሆኑን ገልጿል፡፡ ለእነዚህ ኢትዮጵያውያን መላው የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ከጎናቸው በመሆን አስፈላጊውን ድጋፍ ሊያደርጉላቸው ይገባል ሲል ተናግሯል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲና የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ለጌዴኦ ተፈናቃዮች ድጋፍ ሲያደርግ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ሲሆን ከዚህ ቀደም ዩኒቨርሲቲው 400 ፍራሾች፣ 2000 የመመገቢያ ሰሀኖችና የአልባሳት ድጋፍ ማድረጉ ይታወሳል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት