አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ‹‹ምርምር ለልማት›› በሚል ርዕስ ላይ ያተኮረ 6ኛውን አገር አቀፍ ዓውደ ጥናት ከሚያዝያ 11–12/2011 ዓ/ም አካሂዷል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ተወካይና የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ስምዖን ሽብሩ በፕሮግራሙ መክፈቻ ወቅት እንደተናገሩት  የምርምር ሥራዎች ከፍተኛ ጥራት ያላቸው፣ የመማር ማስተማሩን ሂደት የሚያግዙና የማህበረሰብ ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ ለኑሮ ደረጃ መሻሻል ጉልህ ሚና ያላቸው ሊሆኑ ይገባል ብለዋል፡፡ ዶ/ር ስምዖን አክለው እንደተናገሩት የዩኒቨርሲቲው ራዕይ የሀገርና የዜጎች ራዕይ በመሆኑ የሀገሪቱን ቀዳሚ ችግሮች በመለየት ብሎም የማህበረሰቡን ፍላጎቶች መነሻ በማድረግ ዩኒቨርሲቲው በቂ ምርምሮችን  በተሻለ ሁኔታ እየሠራ ይገኛል፡፡ ምስሉን ለመመልከት ከዚህ ይጫኑ

 

የምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተሾመ ይርጉ እንደገለፁት አውደ ጥናቱ በዩኒቨርሲቲዎችና ምርምር ተቋማት መካከል የእርስ በእርስ ግንኙነትን ማጠናከር፣ የሚከናወኑ የምርምር ሥራዎች የሚገጥሟቸው ተግዳራቶችና የመፍትሄ ሃሳቦች ላይ የዕውቀትና የልምድ ልውውጥ ማድረግን ትኩረት ያደረገ ነው፡፡

ከዕለቱ ተጋባዥ እንግዶች መካከል ፐሮፌሰር መሐመድ አሰን በንግግራቸው  በዩኒቨርሲቲዎች በመማር ማስተማሩ ሥራ ላይ ክፍተት አየፈጠሩ ያሉ ችግሮችን ለመሙላት መንግስት መዋቅራዊ ለወጦችንና የምሁራን ፍልሰትን ለማቆም የሚያስችል ዘዴ ሊቀይስ ይገባል ብለዋል፡፡ ምርምር ለልማት ሞተር የሚሆነው ጥራቱን ጠብቆ ሲሰራ እንደሆነ የተናገሩት ፕሮፌሰሩ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲም የምርምር ሥራዎችን ከቴክኖሎጂ ጋር ማስተሳሰርና ጥናቶቹ የማህበረሰቡን ችግሮች ለመቅረፍ በሚያስችል ደረጃ ላይ መሆናቸውን ማረጋገጥ  አለበት ብለዋል፡፡

ሌላው ተገባዥ እንግዳና ተናጋሪ ዶ/ር ሁሴን ከድር  የምርምር ሥራዎችን ከልማት ጋር ማስተሳሰር ግድ እንደሆነ ገልፀው የምርምር ሥራ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ መሰረት የሆነውን ግብርና በማዘመን ሂደትም ሆነ ሀገሪቱ ወደ ኢንደስትሪ ሽግግር ለማድረግ በምታደርገው ጥረት ውስጥ ጉልህ ሚና ሊጫወት እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡ በዚህ ረገድ የተመራማሪዎች ሚና ትልቅ በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል፡፡

በአውደ ጥናቱ አካል ጉዳተኞች በሥራ ቦታ የሚገጥሟቸው ተግዳራቶች፣ የፖለቲካ አመራር አካላት ዲሞክራሲን ከመገንባትና መልካም አስተዳደርን ከማስፈን አንፃር ያላቸው ሚና፣ ኢትዮጵያ ወደ ውጭ በምትልከው የቡና ምርት ላይ የሚታዩ ችግሮች እንዲሁም የሚዲያ ዘገባ አቀራረብ ጋር ተያይዞ የሚታዩ ክፍተቶች በአውደ ጥናቱ ከቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፎች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡

የኢትዮጵያ ጋዜጠኞችና የሚዲያ ተቋማት ከዘገባ አቀራረብ ጋር ተያይዞ በቀረበው ጥናታዊ ፅሁፍ እንደተገለፀው በ21ኛው  ክፍለ ዘመን የሚዲያ ባለሙያዎች በህዝቦች መካከል አመኔታን የሚያሳጡ ብሎም በህዝቦች መካከል ግጭቶችን የሚፈጥሩ የተዛቡ መረጃዎችን ሲዘግቡ እንደሚስተዋል ተጠቁሟል፡፡ ሚዳያውና ጋዜጠኛው ሙያዊ ስነ-ምግባር የሚጠይቀውን መሠረታዊ ህጎችን በማክበር ሙያዊና ሃገራዊ ግዴታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ በጥናቱ ተጠቁሟል፡፡  አንደ አቅራቢው ገለፃ በእርግጥ የጋዜጠኝነት ሙያ ነፃነትን የሚጠይቅ ሙያ በመሆኑ ጋዜጠኛው ሃሳቡን በትክክል እንዳይገልፅ በመንግስትም በኩል ተፅእኖ ሊደርስበት አይገባም፡፡

ከዓውደ ጥናቱ ተሳታፊዎች መካከል የ2ኛ ዲግሪ ተማሪ የሆነው የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ መምህር አቶ ዶኔ አሊ በሰጠው አስተያየት ከሀገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች የተወጣጡ ምሁራንና ተመራማሪዎች እንዲሁም የተለያዩ ተቋማት የመንግስት አማራር አካላት በተገኙበት የእርስ በእርስ የልምድ ልውውጥ መደረጉ የሀገሪቱን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች ለመፍታት የሚሰጠው ጠቀሜታ የላቀ ነው ብሏል፡፡

በአውደ ጥናቱ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራር አካላት፣ መቀሌ፣ ወላጋ፣ ወልቂጤ፣ ድሬዳዋና አሶሳ ዩኒቨርሲቲዎችን ጨምሮ ከ20 በላይ የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች የተወጣጡ ተመራማሪዎችና የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል ፡:

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት