አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ONLINE እና በE-LEARNING የታገዘ ትምህርት ለመስጠት ምዝገባ ጀመረ

ዩኒቨርሲቲው ONLINE እና በE-LEARNING የታገዘ ትምህርት ለመስጠት ከ Lucy Consulting Engineers PLC (LUCY) ጋር የመግባቢያ ስምምነት በተፈራረመው መሠረት ትምህርቱን ለማስጀመር ምዝገባ መጀመሩ ተገለፀ፡፡ በፕሮግራሙ አጀማመርና አጠቃላይ ሁኔታ ዙሪያ ከኮሌጅ፣ ትምህርት ቤትና ፋካልቲ ዲኖች፣ የትምህርት ክፍል ኃላፊዎችና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር  ግንቦት 6/2011 ዓ/ም ውይይት ተካሂዷል፡፡ ምስሉን ለመመልከት ከዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር የቻለ ከበደ ዩኒቨርሲቲው የመግባቢያ ስምምነቱን ከተፈራረመ በኋላ የርቀትና ተከታታይ ትምህርት ኮሌጅ፣ የድኅረ ምረቃ እና የቤተ-መጻህፍትና መረጃ ዳይሬክቶሬት የሥራ ኃላፊዎች ያሉበት ግብረ ኃይል (Task Force) በማቋቋም የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱን ገልፀዋል፡፡ የዛሬው ውይይትና ሥልጠና የዚሁ ቅድመ ዝግጀት ሥራ አካል እንደሆነ የተናገሩት ዶ/ር የቻለ በዋናነት ሥራውን ለማስጀመር ያግዝ ዘንድ ሂደቱን ከሚመሩና ከሚያስፈጽሙ አካላት ጋር በኮርሶች አሰጣጥና ምዘና እንዲሁም ጥራትና አጠቃላይ ሁኔታዎች ዙሪያ ግንዛቤና የጋራ መግባባት ለመፍጠር ያለመ ነው ብለዋል፡፡

የሉሲ አካዳሚ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር ሀብታሙ መለሰ በውይይቱ ወቅት እንደገለፁት ድርጅታቸው ከዚህ ቀደም ከጂማ ዩኒቨርሲቲ ጋር ተመሳሳይ ሥራዎችን ሲሠራ መቆየቱን አስታውሰው የመግባቢያ ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ በርካታ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ሲሠሩ መቆየታቸውን ገልፀዋል፡፡ ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የተወከለ ቡድን አዲስ አበባ የሚገኘው ድርጅታቸው ያለበትን ሁኔታና መሠረተ ልማት እንደጎበኘ የተናገሩት ዶ/ር ሀብታሙ እስከ አሁን ባለው ሂደትም ትምህርቱን ለመስጠት የሚያስችል ድረ-ገፅ ይፋ በመሆኑ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ተማሪዎች ለመማር ማመልከታቸውን ተናግረዋል፡፡

የትምህርት ጥራት ጉዳይ ለድርድር አይቀርብም ያሉት ዶ/ር ሀብታሙ በዋናነት ትምህርቱ የሚሰጠው በዩኒቨርሲቲው፣ በአገሪቱና በዓለም አቀፍ ደረጃ አሉ በሚባሉ መምህራን መሆኑና የተግባር ልምምድና ቤተ-ሙከራ ትምህርት በሚያስፈልጋቸው ትምህርቶች ተማሪው በቅርበት ባለበት ዩኒቨርሲቲ አልያም አርባ ምንጭ በመምጣት ትምህርቱን መከታተል ይችላል ብለዋል፡፡ በትምህርት አሰጣጥ ወቅት በኢንተርኔት መቆራረጥ ምክንያት ሊፈጠር የሚችል መስተጓጎልን ለመቅረፍ በመምህራን የሚሰጡ ሌክቸሮች ተቀርፀው እንዲቀመጡ ስለሚደረግ ተማሪው ኢንተርኔቱ በመጣበት ማንኘውም ጊዜ ትምህርቱን መከታተል ይችላል ብለዋል፡፡

የተከታታይና ርቀት ትምህርት ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ሠረቀ ብርሃን ታከለ ዩኒቨርሲቲው በርቀት ትምህርት በርካታ ተማሪዎች እንዳሉት ጠቅሰው በተለይ ለርቀት ኮርሶች ሞጁል ዝግጅት፣ ህትመትና ስርጭት ዩኒቨርሲቲው በየዓመቱ ከፍተኛ ወጪ እንደሚያወጣ ገልፀዋል፡፡ ወጪውን ለማስቀረት የመስተማርያ ሞጁሎችን ዲጂታላይዝ በማድረግ ተማሪዎች ONLINE እንዲያገኙ የሚደረግ ከሆነ ጠቀሜታው የጎላ እንደሆነ ገልፀው ለተግባራዊነቱ በቁርጠኝነት መሥራት ይገባል ብለዋል፡፡

የድኅረ-ምረቃ ትምህርት ቤት ዲን ዶ/ር አበራ ኡንቻ በበኩላቸው በቴክኖሎጂ የታገዘ ትምህርት መስጠት ዘመኑ የሚጠይቀው ጉዳይ እንደሆነ ተናግረው በተለይ ዩኒቨርሲቲው የተለያዩ የድኅረ ምረቃ ኮርሶችን ለመስጠት እንግዳ መምህራን በመጋበዝ እንዲሰጡ የሚያደርግ ሲሆን በዚህም ከፍተኛ ወጪ እንደሚያወጣ ተናግረዋል፡፡ ONLINE እና በE-LEARNING የታገዘ ትምህርት እንግዳ መምህራን ኮርሶችን ባሉበት ቦታ ሆነው እንዲሰጡ በማድረግ ዩኒቨርሲቲው የሚያወጣውን ከፍተኛ ወጪ በመቀነስ ረገድ ጉልህ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡

በውይይቱ ወቅት የተለያዩ ጥያቄዎች ተነስተው ምላሽ የተሰጠባቸው ሲሆን ትምህርቱን መከታተል የሚችል በየትኛውም ቦታ የሚገኝ ተማሪ https://www.lucyacademy.com/amu/ ድረ-ገፅ ላይ በመግባት ለምዝገባ ማመልከት እንደሚችልና ከምዝገባ አስከ ምረቃ ያለው የትምህርት አሰጣጥም ሆነ ሌሎች ጉዳዮች በዩኒቨርሲቲው ሕግና ደንብ መሠረት የሚፈፀሙ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት