3ኛው የሥነ-ጽሑፍ ጉባኤ በደማቅ ሁኔታ ተካሄደ


በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ-ጽሑፍ አማርኛ ትምህርት ክፍል እና በማኅበራዊ ሣይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ አዘጋጅነት 3ኛው የሥነ ጽሑፍ ጉባኤ ከግንቦት 2-3/2011 ዓ/ም በጋሞ ዞን ባህል አዳራሽ ታላላቅ ደራሲያንና ገጣሚያን በተገኙበት  በደማቅ ሁኔታ ተካሂዷል፡፡ ምስሉን ለመመልከት ከዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር የቻለ ከበደ በፕሮግራሙ መክፈቻ ላይ እንደተናገሩት ጉባኤው በማንበብ ክሂሎት ዙሪያ ከወጣቶችና ከአካባቢው ህብረተሰብ ጋር በመወያየት ክሂሎቱን የበለጠ ለማዳበር ወሳኝ ከመሆኑም በላይ ቱባ ልምድ ያላቸው ደራሲያንና ገጣሚያን ልምዳቸውን የሚያካፍሉበት ነው፡፡ በተለይ ወጣቶች በማኅበራዊ ድረ-ገፅ አገር የሚያጠፋና ሰላምን የሚያውክ የጥላቻ ጽሑፍ ከሚጽፉና ከባህላቸውና ከወጋቸው የወጡ ነገሮችን ከሚለቁ   አንባቢውን መሠረት አድርገው የተጻፉ፣ አገርን የሚገነቡና ወጣቱን ትውልድ ወደ ተሻለ ደረጃ የሚያደርሱ መረጃዎችን የሰነቁ መጽሐፍትን በማንበብ ትልቅ እውቀት እንዲገበዩና ተተኪ የመሆንን ዓላማ ይዘው ወደፊት እንዲያልሙ ያሻል፡፡ እንደዚሁም መ/ራንና ተሰጥኦ ያላቸው ተማሪዎች የስነ ጽሑፍ ሥራቸውንና ተሰጥኦዋቸውን የሚገልጹበትና የተሻለ መማማሪያ መድረክ በመሆኑ በቀጣይ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ  ቋንቋዎችና ሥነ-ጽሑፍ የአማርኛ ትምህርት ክፍል ኃላፊ መምህርት አፀደ ያረጋል እንደገለፁት የጉባኤው ዓላማ ተሞክሮዎችን በመቅሰም የንባብ ባህል እንዲዳብር ማድረግ፣ በሥነ-ጽሑፍ ዘርፍ ተሞክሮ ያላቸው ሰዎች ልምዳቸውን በማካፈል ተማሪዎችን እንዲያነቃቁ  እንዲሁም  ተማሪዎች ተሰጥኦዋቸውን ወደ ተግባር ለመቀየር እንዲነሳሱ ማስቻል ነው፡፡ በተጨማሪም ተማሪዎችም ሆኑ መ/ራን በተለያዩ የሥነ-ጽሑፍ ሥራዎች ላይ ያላቸውን ግንዛቤ በማሳደግ በነፃነት እንዲወያዩና ሃሳባቸውን እንዲገልፁ ብሎም ተማሪዎች ተለምዷዊ ከሆነው ትምህርት በዘለለ በሥነ-ጽሑፍ ዘርፍ የመሳተፍ ባህላቸው እንዲጎለብት መንገድ ማሳየት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

መ/ርት አፀደ አክለውም ሥነ-ጽሑፍ በወጣቶች ላይ የሚስተዋለውን አላስፈላጊ ሥነ-ምግባር የሚቀይርና ማንነታቸውን እንዲረዱ የሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡ ጉባኤው ተማሪዎችም ሆኑ መ/ራን ያላቸውን እይታና አስተሳሰባቸውን የሚያካፍሉበት መድረክ ነው ያሉት መምህርት አፀደ በቀጣይም የተለያዩ የሥነ ጽሑፍ መድረኮች እንዲዘጋጁ ዩኒቨርሲቲው የበኩሉን አስተዋፅኦ ያበረክት ዘንድም ጠይቀዋል፡፡

‹‹ማንኛውም ሰው በራሱ ሙያ ላይ ታሪክንና ሥነ-ጽሑፍን መጨመር አለበት›› ያለው ጋዜጠኛና ደራሲ ዘነበ ወላ ሥነ-ጽሑፍ ያለፈውን ዘመን እንድናይ ዕድልና ጊዜ የሚሰጠን ከመሆኑም በተጨማሪ  ወደፊት የሚመጣውን እንድንተነብይ አጋጣሚን የሚፈጥር ደስታ የሚገበይበት ጥበብ እንደሆነም ገልጿል፡፡ ሙሉ ሰው ለመሆን ማንበብ ወሳኝ ነው ያለው ደራሲው ተማሪዎች ዓይንና ጆሯቸውን ከፍተው አፋቸውን ዘግተው ማስተዋልና አቅም በፈቀደ መጠን የተለያዩ  ነገሮችን በማንበብ አእምሯቸውን ማጎልበትና አመለካከታቸውን ማስፋት እንዲሁም  ነገሮችን በተለያየ አቅጣጫ ማየትና ጠያቂ ትውልድ ለመሆን መሞከር አለባቸው ብሏል፡፡

በተጨማሪም ከተለያዩ ሱሶችና መሰል ችግሮች ተጠብቀው የመጡበትን ዓላማ ለማሳካት ተግተው እንዲሠሩና ጎን ለጎን የተለያዩ የሥነ-ጽሑፍ ሥራዎችን በማንበብ የገሀዱን ዓለም እውነታዎችን በመረዳት ቀጣይ ህይወታቸውን ማሳመር ይገባቸዋል ብሏል፡፡ በመሆኑም ሁሉም ሰው በቀን 15 ደቂቃ ማንበብ ቢጀምር በሂደት ልምዱ እየዳበረና የማንበቢያ ሰዓቱን እያሻሻለ እንደሚመጣም ከተሞክሮ አንፃር ገልጿል፡፡
በሌላ በኩል ደራሲ ለመሆን ማንበብ፣ በህይወት ውስጥ ማለፍ፣ ማገናዘብ፣ የማኅበረሰቡን ቋንቋ፣ ባህል፣ አመለካከት በወጉ ለመረዳት መሞከር ብሎም ዝንባሌና ጥረት ያስፈልጋል ያለው ዘነበ የምንጽፈው ቁም ነገር ያለውና ዘመን የሚሻገር መሆኑንና ህይወትን በሚገባ በመረዳት ለማኅበረሰባችን መጻፍ አለብን ብሏል፡፡

በፕሮግራሙ ‹‹ዓበይት የአገር አሳሳልና ውክልና በአማርኛ ሥነ ግጥም ውስጥ›› የሚል የዳሰሳ ጥናት በኢትዮጵያ  ቋንቋዎችና ሥነ ጽሁፍ ትምህርት ክፍል መምህር ዘመኑ ሀዲስ የቀረበ ሲሆን ትኩረቱም በአገር ማንነት እና በፆታ ውክልና ላይ ነው፡፡ ይህንንም መሠረት አድርጎ የተለያዩ አከራካሪ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተው ውይይት ተካሂዶበታል፡፡ በተጨማሪም የደራሲያን ወግ በሚል የተለያዩ ጥያቄዎች ተነስተው በደራሲያኑ እና በገጣሚያኑ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

ደራሲና ጋዜጠኛ ዘነበ ወላ፣ ገጣሚ ኤፍሬም ስዩም፣ ገጣሚ መዘክር ግርማና ገጣሚና የመድረክ አስተዋዋቂ ረድኤት ተረፈ አሁን ያሉበት ደረጃ ለመድረስ የተከተሏቸውን መንገዶችና ልምዶች በስፋት የቃኙ ሲሆን የተለያዩ አስተማሪና አዝናኝ ግጥሞችንና ወጎችንም  አቅርበዋል፡፡ በተጨማሪም የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችም ግጥሞቻቸውን አቅርበዋል፡፡

የጉባኤው ታዳሚዎች በሰጡት አስተያየት ዝግጅቱ አስተማሪና አዝናኝ ብሎም በርካታ ልምዶችን የቀሰሙበት፣ ያላቸውን የሥነ ጽሑፍ ዝንባሌ መድረክ ላይ ያሳዩበት በመሆኑ መደሰታቸውን ገልፀዋል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት