በህግ የበላይነትና በህገ-መንግሥት እንዲሁም ፌዴራሊዝምና አገረ-መንግሥት ግንባታ ላይ ስልጠና ተሰጠ

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ቤት ከደ/ብ/ብ/ሕ/ክ/መንግሥት ጠቅላይ አቃቤ ህግ ጋር በመተባበር ‹‹በህግ የበላይነትና ህገ-መንግሥት›› እንዲሁም ‹‹ፌደራሊዝምና ሀገረ-መንግሥት ግንባታ›› በሚል ርዕስ ከግንቦት 5-6/2011 ዓ/ም ድረስ ለፍትህ አካላትና ባለ ድርሻ አካላት ስልጠና ሰጥተዋል፡፡ ምስሉን ለመመልከት ከዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ስምኦን ሽብሩ በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው ዩኒቨርሲቲው በህግና ፍትህ ዘርፍ የሚሰጠውን የማኅበረሰብ አገልግሎት የበለጠ ውጤታማና ተደራሽ ለማድረግ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ መሆኑንና በሌሎች ዘርፎችም ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በተቀናጀ ሁኔታ በመሥራት የላቀ አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የደ/ብ/ብ/ሕ/ክልላዊ መንግሥት ም/ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ አቶ ጥላሁን አማኑኤል በመክፈቻ ንግግራቸው ኢትዮጵያ በአሁኑ  ወቅት እየተከተለች ያለችው የፌዴራል ሥርዓት የአገሪቱ የህጎች ሁሉ የበላይና የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የቃል ኪዳን ሰነድ በተባለው የኢፌዴሪ ህገ-መንግሥት ተደንግጎ የሚገኝ ቢሆንም አሁን እየተካሄደ ካለው ለውጥ ጋር የሚስተዋሉና የሚራመዱ ሀሳቦች የፌዴራል ሥርዓትን እስከመነቅነቅ የሚደርሱ ናቸው ብለዋል፡፡ በመሆኑም የሚወሰኑ ውሳኔዎችና የሚወሰዱ እርምጃዎች በእውቀት ላይ የተመሠረቱ እንዲሆኑና የነቃ ተሳትፎ እንዲኖር፣ ከፅንፈኝነት የፀዳች የሁሉም የሆነች አገርን ለማዝለቅ እንዲሁም ህፀፆችን ለይቶ ለማስተካከል የሚያስችል ግንዛቤ ያስፈልጋል፡፡ ስልጠናው ለዚህ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም ገልፀዋል፡፡

ስልጠናውን የሰጡት የህግ ትምህርት ቤት መ/ር አቶ ዳኛቸው ወርቁ እንደገለፁት የህግ የበላይነት ማለት ህግ የበላይ ሆኖ ሁሉንም ሰው በእኩል ሲያይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የህግ የበላይነት በሌለበት ሁኔታ ሊኖር የሚችለው የሰው ወይም መንግሥትን የሚዘውሩ ፖለቲከኞች የበላይነት ነው፡፡ የህግ የበላይነትን ማስከበር የየትኛውም አገር ተቀዳሚ ተግባርና አገርን እንደ አገር ህልውናዋን አስጠብቆ ለማስቀመጥ ወሳኝ ቅድመ ሁኔታ መሆኑን አሰልጣኙ ገለረጸዋል፡፡

አሰልጣኙ አክለውም በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ገና በእንጭጭ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሂደት ውስጥ ባሉ አገራት የህግ የበላይነት ጉዳይ ትልቁን ቦታ የሚይዝ ሲሆን  የህግ የበላይነት የሚረጋገጠው  ጠንካራ ተቋማት ሲገነቡ ብቻ እንደሆነና  የበላይነቱ ከሌለ ደግሞ አስተማማኝና ዘላቂ ሥርዓት መገንባት እንደማይቻል ጠቁመዋል፡፡ የህግ የበላይነት ከሌለ  አገር የግለሰቦች መፈንጫ፣ ስልጣን የአምባገነኖች እና የመዝባሪዎች መሸሸጊያ ይሆናል፤ ስርዓት አልበኝነት ይነግሳል፤ የአገር ሰላም ይናጋል፤ ዜጎች በሚኖሩበት አካባቢና አገር ነፃነት ተሰምቷቸው እንዳይኖሩ በማድረግ የዕለት ተዕለት ህይወትን ያደናቅፋል፡፡ በየትኛውም ነባራዊ ሁኔታ የህግ የበላይነት ጠንክሮ ባለበት ሁሉ ሥርዓት አልበኝነት ቦታ እንደማያገኝና በተቃራኒው ደግሞ ህግ የሚያስከብረው አካል አቅም ሲያጣ ሥርዓት አልበኝነት እንደሚጠናከር ተናግረው መንግሥት የህግ የበላይነትን ማስጠበቅ ይገባዋል ብለዋል፡፡

ሌላኛው አሰልጣኝ የህግ ትምህርት ቤት መ/ር ደረጀ ማሞ በሰጡት ገለፃ ህገ-መንግሥት የአንድ አገር የበላይ ህግ እንደሆነ በተለምዶ የሚታወቅ ሲሆን የህገ-መንግሥት የበላይነት ስንል በአገሪቱ ውስጥ ህገ-መንግሥቱ ማንኛውንም ሰውና የመንግሥት አካል ወይም ባለስልጣን የመግዛት ወይም የማስገደድ ኃይል አለው ማለት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የህግ የበላይነትን ማስፈኛ መርሆዎች በአንድ አገር ህገ-መንግሥት ውስጥ ተካተው የሚገኙ ሲሆን ዜጎችም እነዚህን በህገ-መንግሥት የተቀመጡና የህግ የበላይነትን ለማጠናከር ወሳኝ የሆኑ ድንጋጌዎችን ማክበርና ማንኛውንም አይነት አለመግባባት ወይም ቅሬታ በህገ-መንግሥቱ በተቀመጠው መሠረት መፍታት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ በማህበረሰብ ብዝሃነት የምትገለፅ ሲሆን በአገሪቱ የሚወጣው ማኛውም ህገ-መንግሥት የህዝብ ቅቡልነት እንዲኖረው ካስፈለገ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎና ውይይት አስፈላጊ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በክልል ርዕሰ መስተዳደር የመልካም አስተዳርና የአካባቢ ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አዳነ ገበየሁ በበኩላቸው ፌዴራሊዝም ሁለትና ከሁለት በላይ መንግሥታት የሚፈጥሩት የሥራ አስተዳደርን ያጣመረ በቃል ኪዳን የሚመሠረትና የሚመራ አጋርነት እንደሆነና ሥርዓቱ አንዱ የሌላውን ቅንነትና አብሮ የመኖር እሳቤን በማመን ላይ የተመሠረተ፣ አንዱ የሌላውን ታሪክ፣ ባህል፣ ቋንቋ፣ ኃይማኖት በማክበርና በመጠበቅ በእኩልነት ላይ የተመሠረተ ሥርዓት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ የፌዴራሊዝም ሥርዓት ከሌሎች ሥርዓተ-መንግስቶች ጋር ያለው ልዩነትና አንድነትን አስመልክተው በስልጠናው ሰፊ ማብራሪያም ሰጥተዋል፡፡

በተጨማሪም በህግ የበላይነትና በህግ መገዛት፣ የህግ የበላይነት መገለጫዎች፣ ስልጣንን መወሰን የስልጣን ክፍፍል፣ የዜጎች ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች መከበር፣ የሥነ-ሥርዓት ህጎች እና የኢፌዴሪ ህገ-መንግሥት የበላይነት የመሳሰሉት ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡
የዩኒቨርሲቲው የህግ ትምህርት ቤት ዲን አቶ ደርሶልኝ የኔአባት ሰልጣኝ ባለሙያዎች ወደታች በመውረድ የህግ ማስረፅ ሥራ እንዲሠሩ አሳስበው ከኃይማኖት ተቋማትና ከአገር ሽማግሌዎች ተወክለው የመጡትም በርካታ ተከታይና ተደማጭነት ያላቸው በመሆኑ ወደ

መጡበት ተቋም ተመልሰው የተከታዮቻቸውን አስተሳሰብ የማስተካከልና የአገሪቱን ሰላምና አንድነት የማስጠበቅ ኃላፊነት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡
ሰልጣኞች በሰጡት አስተያየት ውይይቱ ወቅታዊና መሠረታዊ ጉዳዮች የተዳሰሱበት እና አገሪቱ ያለችበት ሁኔታ ምን እንደሚመስል ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ከመሆኑም በላይ በተነሱት ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በቂ ግንዛቤን እንዲጨብጡ ያስቻላቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት