‹‹የጋራ ትስስር በመፍጠር፣ ችግር ፈቺ የሆነ ጥናትና ምርምር በማድረግና ቴክኖሎጂን በማሸጋገር የአገሪቱን ልማት እናፋጥናለን›› በሚል መሪ ቃል አገር አቀፍ የዩኒቨርሲቲ-ኢንደስትሪ ትስስር ፎረም ሰኔ 1/2011 ዓ/ም በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተካሂዷል፡፡

የዩኒቨርሲቲ ኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ቶሌራ ሴዳ እንደገለጹት የፎረሙ ዓላማ የዩኒቨርሲቲ-ኢንደስትሪ ትስስርን በማጠናከር የተሻለ የቴክኖሎጂ ሽግግርና ማላመድ እንዲሁም ፈጠራን የማጎልበትና የማስፋፋት ተግባራትን በማካተት ለማኅበረሰቡ የላቀ አገልግሎት  እንዲሰጥ ማስቻል ነው፡፡ በተጨማሪም ከኢንደስትሪዎች የሚመነጩ ችግሮች ላይ ጥናትና ምርምር በማድረግ ተጨባጭ መፍትሄዎችን በማቅረብ ችግሮቹ የሚፈቱበትን የጋራ አቅጣጫ ማስቀመጥ ነው፡፡

የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንትና የፕሬዝደንቱ ተወካይ ዶ/ር የቻለ ከበደ ፕሮግራሙን ሲከፍቱ እንደገለፁት ለአንድ አገር ሁለንተናዊ ዕድገት የምርምርና ቴክኖሎጂ ሥራዎች ወሳኝ በመሆናቸው ከመማር ማስተማር ጎን ለጎን ለጥናትና ምርምር እንዲሁም ለማኅበረሰብ አገልግሎት ቁልፍ ሥራዎች ትኩረት በመስጠት በተጠናከረ ሁኔታ መሥራት ያስፈልጋል፡፡

የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ስምዖን ሽብሩ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው የንድፈ ሀሳብ ዕውቀቶችንና ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅና ከኢንደስትሪዎች ጋር በማስተሳሰር ለአገሪቱ ዘላቂ ልማት ተግባራዊ አስተዋፅኦ ለማበርከት የተጣለበትን ኃላፊነት እየተወጣ ይገኛል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ዳንኤል ቅጣው በበኩላቸው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ኢንደስትሪዎችን የሚያግዙ፣ በኢንደስትሪዎች ውስጥ ገብተው መፍትሄ የሚሰጡና ችግሮችን የሚፈቱ ተማሪዎችን ማፍራት አለባቸው፡፡

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የዩኒቨርሲቲ-ኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ሙሉጌታ ዳዲ እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲዎች ከኢንደስትሪዎች ጋር ትስስር መፍጠራቸው የጋራ ጠቀሜታው ጉልህ በመሆኑ ሁለቱም አካላት በትኩረት ሊሠሩ ይገባል፡፡

በፎረሙ የተለያዩ ጥናታዊ ጽሑፎችና የፈጠራ ሥራዎች የቀረቡ ሲሆን ከተለያዩ የኢንደስትሪ፣ ማኑፋክቸሪንግ እና የምርምር ተቋማት ጋር የመግባቢያ ስምምነቶችም ተደርገዋል፡፡
በፕሮግራሙ የምግብ፣ መጠጥ እና መድኃኒት ተቋም፣ የኢትዮጵያ ጨረራ መከላከያ ባለሥልጣን፣ የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ እና ሌሎች ተቋማት ተሳታፊዎች፣ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮች እና ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል፡፡