የዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች ኅብረት ተመራቂ አባላት ሐምሌ 5/2011 ዓ/ም በአባያ ካምፓስ አሸኛኘት ተደርጎላቸዋል፡፡ በዕለቱ የአባያ ካምፓስ የተማሪዎች ኅብረት አባላትና የካምፓሱ አስተዳደር በጋራ ያሠሩት የተማሪዎች ኅብረት መታሰቢያ አደባባይም ተመርቋል፡፡ ምስሉን ለመመልከት ከዚህ ይጫኑ

ፕሮግራሙን የከፈቱት የኮሌጁ ዲን ዶ/ር ፈቃዱ ማሴቦ የተማሪዎች ኅብረት አባላት ከዩኒቨርሲቲው ጎን በመቆም ግቢው ሰላማዊ እንዲሆን፣ ጤናማ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲካሄድ እንዲሁም ሥራዎችን በባለቤትነት በማከናወን ረገድ ትልቅ አስተዋፅኦ ያበረከቱ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ተሳትፎው ለአባላቱ ትልቅ ልምድ የሚያስገኝላቸው እንደሆነ የተናገሩት ዲኑ በቀጣይም ወደ ሥራ ዓለም ሲገቡ ባካበቱት ልምድ ተጠቅመው በፈቃደኝነት ህዝብንና አገርን እንዲያገለግሉ አደራ ብለዋል፡፡

የግብርና ሣይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ይስሃቅ ከቸሮ እንደገለፁት የተማሪዎች ኅብረት፣ ሰላም ፎረም እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በጋራ ባደረጉት ጥረት የትምህርት ዘመኑ የተሳካ፣ የተሻለና ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት የተከናወነበት ሆኗል ብለዋል፡፡ በሌላ በኩል ስኬት የጥረት ውጤት እንደመሆኑ መጠን እራሳቸውን ከወቅቱ ሁኔታዎች ጋር በማጣጣም ለተለያዩ የትምህርት ዕድሎች መዘጋጀትና ብቁ መሆን እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

ዶ/ር ይስሃቅ በተማሪዎች ኅብረት ስም መታሰቢያ አደባባይ መዘጋጀቱ የሚበረታታና ለሌሎች ካምፓሶችም ጥሩ ተሞክሮ እንደሆነ ጠቁመው ለተመራቂ የኅብረቱ አባላት  ቀጣዩ ጊዜ የሰመረ እንዲሆንላቸው መልካም ምኞታቸውን ገልፀዋል፡፡

የተማሪዎች ኅብረት ፕሬዝደንት ተማሪ ቃልኪዳን አባይነህ ተማሪዎች ችግር ፈጣሪ ሳይሆኑ ለመልካም ዓላማ በመቆም ለተግባራዊነቱ መትጋት እንደሚገባቸው ተናግራለች፡፡ በተጨማሪም ተመራቂዎች የአገሪቱ ተስፋ እንደመሆናቸው መጠን ከተቋም ከወጡ በኋላ በማንኛውም መስክ ላይ በመሰማራት በየዘርፉ ባገኙት ዕውቀትና ክህሎት የሚጠቅም ነገር ሊሠሩ ይገባል ብላለች፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት