የ2011 ዓ.ም አጠቃላይ የኮሚዩኒቲ ት/ቤቶች የወላጅ በዓል ሐምሌ 6/2011 ዓ.ም በድምቀት ተከብሯል፡፡ የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ስምዖን ሽብሩ ወላጆች ልጆቻቸውን ት/ቤት ከመላክ ባሻገር በየጊዜው ስለልጆቻቸው የትምህርት ሁኔታና ሥነ-ምግባር ከመምህራኑ ጋር ግንኙነት ሊኖራቸው ይገባል ብለዋል፡፡ ምስሉን ለመመልከት ከዚህ ይጫኑ

የማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በበኩላቸው ከ2 ዓመታት ወዲህ ከተማሪዎች ውጤትና ከሥነ-ምግባር አኳያ በት/ቤቱ በሚፈለገው ደረጃ መሻሻሎች መታየታቸውን ገልጸዋል፡፡

የ2ኛ ደረጃ ት/ቤት ር/መምህር አቶ ካምቦ ከተማ ባቀረቡት ሪፖርት እንደተብራራው የፈተና ሥርዓቱን ከኩረጃ ነፃ ለማድረግ የተወሰደው ጠንካራ አቋም በተማሪዎች መካከል ከፍተኛ የውድድር መንፈስ ከመፍጠሩም ባሻገር ተሣትፎ እንዲጨምር አድርጓል፡፡ በዚህም 60% በታች አማካይ ውጤት የሚያመጡ ተማሪዎችን በከፍተኛ ሁኔታ ዝቅ ማድረግ ተችሏል፤ በክላስተር ከ4-8ኛ ክፍል በተደረገው የጥያቄና መልስ ውድድር ከተሳተፉ 15 ተማሪዎች 12ቱ ውድድሩን ያሸነፉ ሲሆን በሁሉም የክፍል ደረጃዎች የ1ኛነት ደረጃ አግኝተዋል፡፡

የወላጅ ድጋፍን በተመለከተ በተደጋጋሚ የሚያረፍዱም ሆነ የሚቀሩ ተማሪዎች ወላጆች ከት/ቤቱ ጋር በቅንጅት በመደገፋቸው የተሻለ የባህርይና የውጤት ለውጥ ማምጣት ችለዋል፡፡ በደንብ ልብስ፣ በፀጉር አቆራረጥ፣ በውበት ቀለሞችና በተንቀሳቃሽ ስልክ አጠቃቀምና ሌሎችም የሥነ-ምግባር ሁኔታዎች ባለፉት 2 ዓመታት መሻሻሎች መታየታቸው በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡

ወላጆች በሰጡት አስተያየት የመምህራንን አቅም ከመገንባት አኳያ ሥልጠናዎች ቢዘጋጁ፣ በተለያዩ ምክንያቶች ሰዓት በማርፈድ ውጪ የሚቆዩ ተማሪዎች አልባሌ ቦታ እንዳይውሉ ወደ ውስጥ በማስገባት የምክር አገልግሎት ቢሰጥ፣ ሰርቪስ አጠቃቀም ላይ ማሻሻያ ቢደረግ የሚሉና ሌሎችም ጥያቄዎችና አስተያየቶችን ሰጥተዋል፡፡

በፕሮግራሙ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ መምህራንና የተማሪ ወላጆች የተገኙ ሲሆን 1-3 ለወጡ ከ1ኛ-12ኛ ክፍል ተማሪዎች ሽልማት እንዲሁም የላቀ ውጤት ላመጡ ተማሪዎች ልዩ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት