አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከጋሞ ዞን፣ ከአ/ምንጭ ከተማ አስተዳደርና ከዩኒቨርሲቲው ለተወጣጡ የሴክተር መስሪያ ቤት ሠራተኞች ከነሐሴ 3/2011 ዓ/ም ጀምሮ ሲሰጥ የነበረው የዲጂታል ቴክኖሎጂ አጠቃቀም (Digital Literacy) ስልጠና የመጀመሪያው ዙር በስኬት ተጠናቀቀ፡፡ምስሉን ለመመልከት ከዚህ ይጫኑ


የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ስምዖን ሽብሩ እንደገለፁት ሥልጠናው የዩኒቨርሲቲው የ3ኛ ዙር የ100 ቀናት ዕቅድ አካል ሲሆን ለተግባሩ ስኬታማነት ከኮምፕዩተር ሳይንስ ፋካልቲና ከመረጃና ኮሚዩኒኬሼን ዳይሬክቶሬት የተወጣጡ 50 አሠልጣኞች እንዲሁም በዩኒቨርሲቲው ሶስት ካምፓሶች የሚገኙ 23 የኮምፕዩተር ላቦራቶሪዎች ተዘጋጅተው ሥልጠናው ተሰጥቷል ብለዋል፡፡
ሥልጠናው አምስት ሞጁሎች ያሉት ሲሆን በዋናነት በመሠረታዊ የኮምፕዩተር ክህሎት፣ በአለም አቀፍ የመረጃ መረብ አጠቃቃም፣ በኮምፒውተር ፕሮግራሞች፣ በኮምፒወተር ሚስጥራዊነትና መረጃ አያያዝ (Computer Security and Privacy) እና ዲጂታል የኑሮ ዘይቤ በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ በተግባር ተደግፎ ለ25 ሰዓታት የተሰጠ መሆኑን ዶ/ር ስምዖን ተናግረዋል፡፡ ሥልጠናው የሠራተኞችን የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ችሎታ ከማሳደግ አኳያ ጉልህ ሚና እንደሚኖረው የተናገሩት ዶ/ር ስምዖን በየመስሪያ ቤቱ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲኖር ከማድረግ ረገድም የራሱን እሴት ይጨምራል ብለዋል፡፡
ከሥልጠናው ተሳታፊዎች መካከል ከጋሞ ዞን አስተዳደር ጽ/ቤት የመጡት ወ/ሮ ሰናይት ሙሉጌታ እንዳሉት ከዚህ በፊት ስለ ኮምፕዩተር አጠቃቀም ያላቸው ግንዛቤ አነስተኛ መሆኑን ገልፀው በሥልጠናው መሠረታዊ ዕውቅት ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡ በየመስሪያ ቤቱ ያሉ የኮምፕዩተር አጠቃቀም ክህሎት ክፍተት ያለባቸው በርካታ ሠራተኞች መሰል ሥልጠናዎችን እንዲያገኙ ቢደረግ ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል፡፡
ሌላኛው ሰልጣኝ በአ/ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሬጂስትራር ባለሙያ የሆኑት አቶ አንዷለም ደጉ በበኩላቸው በሥልጠናው አዳዲስ ዕውቀቶችን እንዳገኙ ገልፀው ጊዜው የቴክኖሎጂና በየጊዜው አዳዲስ ነገሮች የሚፈጠሩበት በመሆኑ መሰል የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠናዎች ሠራተኞችን ከዘመናዊ አሠራሮች ጋር ለማዛመድ ያላቸው ፋይዳ ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡
በሥልጠናው የመጀመሪያው ዙር ከተለያዩ ሴክተር መስሪያ ቤቶች እንዲሁም ከጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የተወጣጡ ከ1,000 በላይ ሠልጣኞች ሥልጠናውን ተከታትለዋል፡፡ ሁለተኛው ዙር ሥልጠና ተሰጥቶ ሲጠናቀቅ በተመሳሳይ ሁኔታ በሳውላ ካምፓስ ሥልጠናው የሚቀጥል ይሆናል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት