አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከቤልጅየሙ የ KU LEUVEN ዩኒቨርሲቲ ጋር በምርምር፣ በአቅም ግንባታ ስልጠና፣ በመማር ማስተማርና በቴክኖሎጂ አጠቃቀም ዙሪያ በጋራ ለመስራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ነሐሴ 15/2011 ዓ/ም ተፈራርሟል፡፡ በዕለቱ የ KU LEUVEN ዩኒቨርሲቲ  ፕሬዝደንት /ሬክተር/ ፐሮፌሰር LUC Sels /ሉክ ሴልስን/ ጨምሮ ሌሎች የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ የሥራ አመራሮችና ፐሮፌሰሮች የተገኙ ሲሆን የ ICT መሰረተ- ልማቶችን፣ ቤተ-ሙከራዎችንና በጫሞ ሐይቅ ላይ የሚሰሩ የምርምር ሥራዎች የመስክ ምልከታም አካሂደዋል፡፡click here to look the picture
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ዩኒቨርሲቲው ከዚህ ቀደም በIUC ፕሮግራም አማካይነት ከ KU LEUVEN ዩኒቨርሲቲ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ለ4 ዓመታት በጋራ ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰው ይህም ስምምነት ከዚህ ቀደም የነበረውን ትብብርና ግንኙነት ለማጠናከርና ለማጎልበት የሚያግዝ ነው ብለዋል፡፡ እንደ ዶ/ር ዳምጠው ገለፃ በስምምነቱ መሰረት የመምህራን  የትምህርት ዕድል፣ ምርምርን ማዕከል ያደረገ የትምህርት አሰጣጥን ማጎልበት  እንዲሁም የማህበረሰቡን ችግር ለመፍታት የሚያስችሉ የምርምር ሥራዎችን በመስራት ላይ ሁለቱ ተቋማት በጋራ ይሠራሉ ብለዋል፡፡ አስካሁን ባለው የሁለቱ ተቋማት ግንኙነትና ትብብር ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ መስኮች  በርካታ ጥቅሞችን ማግኘቱን ዶ/ር ዳምጠው ተናግረዋል፡፡
የምርምርና ማህበረሰብ አገ/ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ስምዖን ሽብሩ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ካላቸው ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመማር ማስተማር፣ በምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት እንዲሁም ቴክኖሎጂ ሽግግር ዙሪያ በጋራ እየሰራ ሲሆን ለዚህም ቤልጂየም ሀገር ከሚገኙ 5 ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በጋረ እየሰራ  መሆኑ አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡ የአሁኑ ስምምነትም ተጨማሪ ፕሮግራሞችንና ፕሮጀክቶችን በጋራ ቀርፆ ከመስራት፣ የጋራ ትምህርት ፕሮግራሞችን ቀርፆ ከማስተማር፣ በጋራ ፈንዶችን በማፈላለግ ረገድ ጉልህ ድርሻ  ይኖረዋል ብለዋል፡፡ ከነዚህ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር እ.እ.አ ከ2011 ጀምሮ ግንኙነት መጀመሩን የገለፁት ዶ/ር ስምዖን እስካሁን ባለው ሂደት 19 መምህራን የ3ኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ሲሆን 4 መምህራን የ3ኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን ጨርሰው ዩኒቨርሲቲውን እያገለገሉ ናቸው ብለዋል፡፡ በቅርቡ 2 መምህራንም ትምህርታቸውን ጨርሰው ይመጣሉ ብለዋል፡፡
ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ የመጀመሪያቸው እንደሆነ የገለፁት የ KU LEUVEN ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት  ፕሮፌሰር Luc Sels ወደ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ያደረጉት ጉብኝት ዋና ዓላማ በሁለቱ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል በመምህራን አቅም ግንባታ ስልጠና፣ በምርምር፣ በቤተ-ሙከራዎችና ICT መሰረተ-ልማት ማሟላት ላይ የተጀመረውን ድጋፍና ግንኙነት ለማጠናከር ነው ብለዋል፡፡ በሁለቱ ተቋማት መካከል በነበረው ትብብርና ግንኙነት በአጭር ጊዜ ውስጥ በዩኒቨርሲቲው የታዩ ለውጦችና ሥራዎች አበረታች መሆናቸውን የተናገሩት ፕሬዝደንቱ ይህም ለዩኒቨርሲቲው የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው ለመቀጠል አሳማኝ ሆነው እንዳገኙት ተናግረዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲያቸው ከተመሰረተ 594 ዓመታትን እንዳስቆጠረ የተናገሩት ፕሬዝደንቱ ዩኒቨርሲቲያቸው በቅርቡ በፈጠራ ሥራዎች በተደረገ ውድድር ከአውሮፓ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል 1ኛ  እንዲሁም በዓለም 7ኛ ደረጃን ማግኘቱን ተናግረዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲያቸው በሁሉም መስክ ያለውን ልምድ ለአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ለማካፈል ዝግጁ ነው ያሉት ፕሮፌሰር ሉክ ዩኒቨርሲቲው በተለይ በአካባቢው የሚገኙ እንደ ጫሞ ሐይቅ ያሉ የተፈጥሮ ሀብቶችን ከአደጋ ለመታደግ የጀመረውን የምርምርና የተግባር ሥራ አጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል፡፡ ለዚህም የ KU LEUVEN ዩኒቨርሲቲ ድጋፍ  እንደማይለየው ገልፀዋል፡፡
በሀገራችን ከአቅም ውስንነት ጋር ተያይዞ በሁሉም መስኮች ሊባል በሚችል ደረጃ በርካታ ችግሮች መኖራቸውን የጠቀሱት የ AMU-IUC ፕሮግራም ኃላፊና የውሃ ሥነ-ምህዳር ተመራማሪው ዶ/ር ፋሲል እሸቱ እነዚህን ችግሮች በሳይንሳዊ ምርምር ታግዞ ለመፍታት እንደ KU LEUVEN ካሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ የልህቀት ማዕከል ከሆኑ ተቋማት ጋር በጋራ መስራት የግድ ነው ብለዋል፡፡ IUC ፕሮግራምም ይህንን መነሻ በማድረግ በውስጡ 6 የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ ከነዚሁ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በትብብር እየሰራ እንደሆነም ገልፀዋል፡፡ ፕሮጀክቶቹ ጥናት ላይ ብቻ ያተኮሩ አለመሆናቸውን የተናገሩት ዶ/ር ፋሲል ጎን ለጎን ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመተባበር በጫሞ ሐይቅ ላይና በሌሎች ቦታዎች የእንተርቬንሽን ሥራዎች እየተሰሩ ናቸው ብለዋል፡፡
በፕሮግራሙ ላይ ለእንግዶቹ የተለያዩ የባህላዊ አልባሳት ስጦታዎች የተበረከቱ ሲሆን የ KU LEUVEN ዩኒቨርሲቲም በፕሬዝደንቱ አማካይነት የ AMU-IUC ፕሮግራምን በኃላፊነት እየመሩ ለሚገኙት ለዶ/ር ፋሲል እሸቱ ስጦታ አበርክቷል፡፡ በተጨማሪም የልዑክ ቡድኑ ከዩኒቨርሲቲው አመራሮች ጋር በመሆን በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ የችግኝ ተከላም አከናውኗል፡፡
ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት