የሁሉ አቀፍ ሴክተር ዳይሬክቶሬት በዩኒቨርሲቲው ከሚገኙ 6 ካምፓሶች ለተወጣጡ 40 የክሊኒክ ባለሙያዎች እና በዳይሬክቶሬቱ አዲስ ለተመደቡ ባለሙያዎች በኤች አይ ቪ/ኤድስና ስነ-ተዋልዶ ዙሪያ  ስልጠና ሰጥቷል፡፡click here to look the picture
የሁሉ አቀፍ ሴክተር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ መርክነህ መኩሪያ እንደገለፁት የስልጠናው ዓላማ የባለሙያዎችን አቅም በማጎልበት በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ትግበራ እንዲያካሂዱና ስልጠናውን መሠረት በማድረግ የክፍሉ ሥራ በተሳለጠ ሁኔታ እንዲከናወን እንዲሁም የባለሙያዎችን ተነሳሽነት በመጨመር የክፍሉ ተግባራት በተቀመጠው ዕቅድና አቅጣጫ መሠረት በመተግበር ውጤታማ እንዲሆኑ ማስቻል ነው፡፡ በተጨማሪም  የሀገሪቱን የኤች አይ ቪ/ኤድስ ስርጭት ለመግታት በሚከናወነው ተግባር ላይ ትልቁን ድርሻ እንዲወጡ ማብቃት ነው ብለዋል፡፡
የህክምናና ጤና ሣይንስ ኮሌጅ መ/ር ማናዬ ይሁን በስነ-ተዋልዶ ጤናና በፆታዊ ጥቃት ላይ ሥልጠና የሰጡ ሲሆን የስነ-ተዋልዶ ጤና ችግር በአብዛኛው በተማሪዎች ላይ የሚስተዋል ሲሆን ይህን ተከትሎ  ያልተፈለገ እርግዝና፣ ጥንቃቄ የጎደለው ውርጃ፣ የአባላዘር በሽታና መሰል ችግሮች ይከሰታሉ ብለዋል፡፡  አሰልጣኙ ተገዳ ለተደፈረች፣ እርግዝናው ከቤተሰብ ወይም ከስጋ ዘመድ ከተፈጠረ፣ ፅንሱ በእናቲቱ ህይወት ላይ ችግር የሚያመጣና አሳሳቢ ከሆነ፣ ፅንሱ ችግር ካለበት እንዲሁም እናቲቱ በአካልም ሆነ በአዕምሮ ዝግጁ ሆና ልጇን ማሳደግ የማትችል ከሆነ ፅንሱን ህጋዊ በሆነ መንገድ ማቋረጥ ይቻላል ብለዋል፡፡
ሌላኛው አሰልጣኝ  የህክምናና ጤና ሣይንስ ኮሌጅ መ/ር ድረስልኝ ምስክር 58 በመቶ ያህል ተማሪዎች አደንዛዥ ዕፅን መጠቀም የሚጀምሩት ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ከገቡ በኋላ እንደሆነ በጥናት የታወቀ መሆኑን ገልፀው ተማሪዎች ወደ እነዚህ ተግባራት የሚገቡት ለጥናት ትኩረትን ለማሰባሰብና ማህበራዊ ግንኙነትን ያጠናክራል በሚል ምክንያት መሆኑን ጥናቶች ያመላክታሉ ብለዋል፡፡
በስልጠናው ወቅት በኤች አይ ቪ/ኤድስና አደንዛዥ ዕፆች ላይ ተማሪዎች ያላቸው ግንዛቤ ምን እንደሚመስልና ባለሙያዎቹ በምን መልኩ እንደሚደግፏቸው  በሰፊው  ውይይት የተደረገ ሲሆን በቀጣይም የህብረተሰብ ጤና ትምህርት ክፍል፣ ሁሉ አቀፍ ሴክተር ዳይሬክቶሬትና ክሊኒክ ባለሙያዎች በጉዳዩ ላይ በጋራ ሊሰሩ እንደሚገባ አጽንኦት ተሰጥቶበታል፡፡
ሰልጣኞች በሰጡት አስተያየት ተማሪዎች በኤች አይ ቪ/ኤድስ፣ በአባላዘር በሽታዎችና እርግዝና በመከላከል ረገድ እንዲሁም በህገ ወጥ መንገድ ፅንስን በማቋረጥ ዙሪያ ላይ ያላቸው ግንዛቤ ከቀድሞ እየተሻሻለና እየጎለበተ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡ በአንፃሩም የኤች አይ ቪ/ኤድስ መመርመሪያ መሳሪያ ዕጥረት በመኖሩ የታሰበውን ያህል የምርመራ አገልግሎት እየተሰጠ አለመሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ 
ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት