የዩኒቨርሲቲው የበጎ አድራጎትና የነፃ ፈቃድ አገ/ማስ/ጽ/ቤት ከዩኒቨርሲቲው አልሙናይ እና በጎ አድራጎት ማዕከል ጋር በጋራ በመሆን ለልማት ሙሉ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት 216 ወንበርና ጠረጴዛ እንዲሁም 15 ጥቁር ሰሌዳዎችን አሠርቶ  አበርክቷል፡፡

የበጎ አድራጎትና የነፃ ፈቃድ አገ/ማስ/ጽ/ቤት ኃላፊ መ/ርት ፍቅርተ ስዩም እንደገለፁት የቁሳቁስ ልገሳው ዓላማ  ለተማሪዎች የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን በማሟላት ምቹ የመማር ማስተማር ሂደትን መፍጠርና የመ/ራንን የማስተማር ተነሳሽነት ማሳደግ ነው፡፡ ምስሉን ለማየት ከዚህ ይጫኑ

የበጎ አድራጎት ማዕከል ተወካይ እና አልሙናይ አቶ አንተነህ ዘሪሁን በፕሮግራሙ ላይ ባቀረቡት ሪፖርት እንደጠቆሙት ለዚህ በጎ ተግባር የአ/ም/ዩ አልሙናይ ከሆኑት አቶ አንዋር ሰኢድ 222,000 /ሁለት መቶ ሃያ ሁለት ሺ ብር/ እና ከዶ/ር ተመስገን ማርቆስ 44,750 /አርባ አራት ሺ ሰባት መቶ ሃምሳ ብር/ እንዲሁም የቀድሞ የ/አ/ም/ዩ ፕሬዝደንት ከነበሩት ዶ/ር ታረቀኝ ታደሰ 5,000 /አምስት ሺ ብር/ በድምሩ 271,750 / ሁለት መቶ ሰባ አንድ ሺ ሰባት መቶ ሃምሳ ብር / ተሰብስቧል፡፡ ከተሰባሰበው ገንዘብ 266,250 /ሁለት መቶ ስልሳ ስድስት ሺ ሁለት መቶ ሃምሳ ብር / ወጪ ተደርጎ ወንበርና ጠረጴዛ(ዴስክ) እና  ጥቁር ሰሌዳ ተሠርቶ ለት/ቤቱ ሊበረከት ችሏል ብለዋል፡፡

ጥራት ያለው ትምህርትን ለማዳረስና ምቹ የትምህርት አካባቢን ለመፍጠር የህብረተሰብ ተሳትፎ ዋና ጉዳይ ነው ያሉት የዞኑ ት/ቤቶች ጽ/ቤት ኃላፊና የአ/ምንጭ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ማዶ መንገሻ የተለያዩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችን  በማስተባበርና ችግሮችን በመረዳት መሠረታዊ ግብዓቶች እንዲሟሉ ያደረጉ የዩኒቨርሲቲው በጎ አድራጎትና ነፃ ፈቃድ አገ/ማስ/ጽ/ቤት፣ የአልሙናይ ማስ/ጽ/ቤት እና የበጎ አድራጎት ማዕከልን በዞኑ ት/ቤቶች ጽ/ቤት ስም የላቀ ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል፡፡ ጽ/ቤቱ የተለያዩ ክፍተቶችን ለመቅረፍ የበኩሉን ሚና እንደሚወጣም ተናግረዋል፡፡

የት/ቤቱ ር/መ/ር አቶ አዳነ ገዛኸኝ እንደተናገሩት ማኅበረሰቡ ቀርቦ በት/ቤቱ ውስጥ የሚታዩ ክፍተቶችን መጠየቅ፣ የበኩሉን ድርሻ መውሰድ እንዲሁም በጋራ መሥራትና ት/ቤቱን ማልማት ይገባዋል ብለዋል፡፡ የተከናወነው ተግባር ለሌሎችም ምሳሌ የሚሆንና ሊበረታታ የሚገባው በመሆኑ ይህንን በጎ አስተዋፅኦ ላበረከቱ ድርጅቶችና አስተባባሪዎች ምስጋና አቅርበው በቀጣይም በጋራ በመሆን ተማሪዎችን በመልካም ሥነ-ምግባር ለማነጽ እንሠራለን ብለዋል፡፡

የወመህ ሰብሳቢ አቶ እጅጉ የማነህ ወንበርና ጠረጴዛዎቹ በአግባቡ ካልተያዙ በአጭር ጊዜ መበላሸታቸው ስለማይቀር ተማሪዎች በአግባቡ እንዲገለገሉበት በተለያዩ አጋጣሚዎች ማስታወስና ክትትል ማድረግ ያሻል ብለዋል፡፡ በቀጣይ ት/ቤቱን ምቹና ሳቢ ለማድረግ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ለት/ቤቱ እድገት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ሊያበረክቱ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

ቀድሞ የነበረው የመቀመጫ እጥረት በመቀረፉ መደሰታቸውን የገለፁት የፕሮግራሙ ታዳሚዎች በቀጣይ የአካባቢውን ወጣቶች በማስተባበር ተማሪዎች አልባሌ ቦታዎች ላይ እንዳይውሉ በጋራ በመሥራት ት/ቤቱንና ተማሪዎቹን ለመለወጥ የተሻሉ ነገሮችን እንሠራለን ብለዋል፡፡ በተጨማሪም መምህራን በአዲሱ የትምህርት ሥርዓት ተማሪዎችን ለመቅረፅና በመልካም ሥነ-ምግባር ለማነፅ ከፍተኛ ተነሳሽነት ሊኖራቸው እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡