የዩኒቨርሲቲው RUNRES ፕሮጀክት ስዊዘርላንድ ከሚገኘው ETH Zurich ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ከመስከረም 13 - 14/ 2012 ዓ/ም ፕሮግራሙን ማስጀመሪያ የምክክር መድረክ በኃይሌ ሪዞርት አካሂዷል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ስምኦን ሽብሩ እንደገለፁት ፕሮጀክቱ በሙዝ እሴት ሰንሰለት ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሠራ ሲሆን ዓላማው ገጠርና ከተማን በምግብ እሴት ሰንሰለት በማገናኘት የአካባቢውን የምግብ ደኅንነትና ልማት ማሻሻልና መጠበቅ፣ የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ ማሻሻል እና በምግብ ራስን ለመቻል በሚደረጉ አገራዊ ጥረቶች ላይ የበኩሉንን ድርሻ መወጣት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ምስሉን ለማየት ከዚህ ይጫኑ

ፕሮጀክቱ በ4 የአፍሪካ አገሮች ማለትም በኢትዮጵያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሩዋንዳና ኮንጎ ላይ የሚሠራ፣ የ8 ዓመት ቆይታ ያለው እና በ2 ዙር የተከፈለ ሲሆን ለመጀመሪያው ዙር 4 ዓመታት 14 ሚልየን ብር በጀት ተመድቦለት ግንቦት/2011 ዓ/ም ፀድቆ ወደ ሥራ መገባቱን ዶ/ር ስምኦን ገልፀዋል፡፡ የገንዘብ ድጋፉ ከስዊዝ ልማትና ተራድኦ ድርጅት የተገኘ ሲሆን ፕሮጀክቱን የሚያስተባብረው ስዊዘርላንድ የሚገኘው ETH Zurich ዩኒቨርሲቲ ነው ብለዋል፡፡

የRUNRES ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ አቶ አባይነህ ፈይሳ እንደገለፁት ፕሮጀክቱ ገጠሩ እስካሁን ከተማውን እየመገበ እንደ መሆኑ መጠን ከተማውም ገጠሩን መመገብ አለበት የሚል ዓላማ የሰነቀ ሲሆን አካባቢን ከመጠበቅ ባሻገር የእሴት ሰንሰለትን በመጨመር ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ነው ብለዋል፡፡ በተጨማሪም ሙዝ አምራች አርሶ አደሩ ተረፈ ምርቱን በሣይንሳዊ መንገድ ተጠቅሞ ማሳው ላይ እንዲመልሰው፤ በአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ያሉ ሙዝ አምራች አርሶ አደሮችን ከከተማው ነዋሪዎች ጋር በማስተሳሰር ገጠሩ ከተማውን ሲመግብ ከተማው በበኩሉ ንጥረ ነገር ያላቸውን ተረፈ ምርቶች ወደ ገጠሩ እንዲመልስ እንዲሁም የመፀዳጃ ቤት ቆሻሻዎችን በሣይንሳዊ መንገድ ማዳበሪያ አድርጎ ለምርታማነት በመጠቀም አርሶ አደሮቹ የተሻለ ምርት አምርተው ለአገር ውስጥ እና ለውጭ አገራት ገበያዎች እንዲያቀርቡ ለማብቃት ነው፡፡ በዚህም የአካባቢ ንፅህና ይጠበቃል፤ አርሶ አደሩ የተሻለ ምርትና ምርታማነቱን ያረጋግጣል እንዲሁም ለወጣቱ ሰፊ የሥራ ዕድልን ይፈጥራል ብለዋል፡፡

የፕሮጀክቱ ዋና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ጆሃን ሲክስ የውኃ ዘላቂ ልማት በማረጋገጥ ጥራት ያለው ውኃ ለሁሉም እንዲዳረስ ማድረግ፣ የምግብ ዋስትናን ከገጠር እስከ ከተማ ማረጋገጥ እንዲሁም የገጠርና የከተማ ቆሻሻ መልሶ በመጠቀም አገልግሎት እንዲሰጥ ማድረግ የፕሮጀክቱ ግብ መሆኑንና አርሶ አደሩ ቆሻሻን ወደ ማዳበሪያነት በቀላሉ የሚለውጥበትን መንገድ በማስተማር የግብርና ምርትን ጥራት ማሻሻል እንደሚቻል ገልፀዋል፡፡

በአ/ምንጭ ከተማ አስተዳደር ማዘጋጃ ቤት የሳኒቴሽን ሥራዎች የፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ እንድሪያስ ኡልቶ በበኩላቸው ማኅበረሰቡ በቆሻሻ አሰባሰብ፣ አወጋገድና መልሶ ጥቅም ላይ በማዋል ረገድ የግንዛቤ ክፍተት ያለበት በመሆኑ መሠረታዊ የአመለካከት ለውጥ እንዲመጣ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የበለጠ ሊሠራ እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡ በተጨማሪም ከየአካባቢያችን የሚወጣውን ቆሻሻ በአግባቡ ከያዝነው ጥቅም ላይ ስለሚውል ከቤት ጀምሮ የሚበሰብሱና የማይበሰብሱ ቆሻሻዎችን በማሰባሰብ እና በመለየት ወደ ተፈላጊው ስፍራ ለማስተላለፍ እንዲሁም ቆሻሻውን ለሚያሰባስቡት ማኅበራት ተገቢውን ክፍያ በወቅቱ በመክፈል ዙሪያ የነቃ የአመለካከት ለውጥ እንዲኖር ህብረተሰቡ ትኩረት መስጠት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት