ለቤተ-መጽሐፍትና መረጃ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ነባርና አዲስ ሠራተኞች ሥልጠና ተሰጠ

የዩኒቨርሲቲው ቤተ-መጽሐፍትና መረጃ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት በአዲሱ የነጥብ ሥራ ምዘናና ደረጃ አወሳሰን (JEG) በሥሩ በተለያዩ የሥራ ክፍሎች ለተመደቡና ለነባር 170 ሠራተኞች የቤተ-መጽሐፍት ዓይነቶችና ምንነት፣ አደረጃጀት፣ ህግና ደንብ፣ አገልግሎት አሰጣጥ፣ ደንበኛ አያያዝ፣ የቴክኒክ ክፍሎች እንዲሁም ዲጂታላይዜሽንና አውቶሜሽን፣ ዶክዩሜንቴሽን እና ማጣቀሻ በሚሉ ርዕሶች ላይ ጳጉሜ 4-5/2011 ዓ/ም የሥራ ላይ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ ምስሉን ለማየት ከዚህ ይጫኑ

የዳይሬክቶሬቱ የደንበኞች አግልግሎት ቡድን መሪና የዳይሬክተር ተወካይ አቶ እንግዳ አሰፋ ሥልጠናው የሠራተኞችን አቅም በማጎልበት ለተማሪዎች፣ ለተማራማሪዎች፣ ለአስተዳደር ሠራተኞች እና በአጠቃላይ ወደ ዩኒቨርሲቲው ለሚመጡ ደንበኞች ቀልጣፋና በቴክኖሎጂ የተደገፈ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡

እንደ አቶ እንግዳ ገለጻ መረጃ የሰው ልጅ አይቶ ወይም አንብቦ ሊረዳው በሚችልና ትርጉም በሚሰጥ መልኩ ተቀናብሮ ስለ አንድ ጉዳይ እውቀት ሊያስጨብጥ የሚችል፣ በወቅቱ የተሰበሰበና የተደራጀ እንዲሁም በተፈለገው ጊዜ አገልግሎት ላይ የሚውል ነው፡፡

የቤተ-መጽሐፍትና መረጃ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት የ6ቱም ካምፓስ ዶክዩሜንቴሽን ቡድን መሪ ወ/ሮ ወለቱ ገብሬ በበኩላቸው ሥልጠናው የተጠቃሚዎችን ፍላጎት መሠረት ባደረገ መልኩ መረጃዎችን በማሰባሰብና በማደራጀት ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት እንዲቻል ባለሙያዎችን የሚያበቃ መሆኑን ገልዋል፡፡

ከተሳታፊዎች መካከል ወ/ሪት ቆንጂት ቆልቻ ሥልጠናው በሥራ ላይ የሚገጥማቸውን ችግር ለመፍታት የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሠልጣኝ አቶ ዘሪሁን ድርባቤ በበኩላቸው በተለይ በሙያዊ ሥነ-ምግባር፣ በውስጠ ደንብ፣ በደንበኛ አያያዝና በመረጃ አያያዝ በተግባር የታገዘ ትምርት እንዳገኝ አግዞኛል ብለዋል፡፡

ከስልጠናው ተሳታፊዎች በርካታ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ተነስተው ምላሸ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት