የ2012 ዓ/ም አገራዊ የከፍተኛ ጥምህርት ተቋማት ውይይት በዩኒቨርሲቲው ተካሄደ

‹‹ለሠላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት መስፈን የበኩላችንን ድርሻ እንወጣለን›› በሚል መሪ ቃል የዩኒቨርሲቲው መምህራንና የአስተዳደር ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች አገራዊ የማኅበረሰብ ውይይት መስከረም 14 ተካሂዷል፡፡ ምስሉን ለማየት ከዚህ ይጫኑ

የ2011 ዓ/ም ዕቅድ አፈፃፀምና የ2012 ዓ.ም ዕቅድ፣ በፍኖተ ካርታ ጥናት ግኝት መሠረት ተቋማትን በተልዕኮና በልህቀት ልየታ አተገባበርና ፋይዳው፣ የመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎች የሚወስዷቸው የትምህርት ዓይነቶችና ፋይዳቸው፣ ሠላማዊ የመማር ማስተማር ሂደትን ማረጋገጥና ማዝለቅ፣ የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ሚናና በየደረጃው ያለውን ኃላፊነትና ተጠያቂነት ማረጋገጥ፣ የመምህራንና የተማሪዎች ዲስፕሊን መመሪያ የውይይቱ ይዘቶች ናቸው፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ እንደገለጹት የውይይቱ ዓላማ በ2012 የትምህርት ዘመን ህግና ሥርዓትን በዩኒቨርሲቲው የበለጠ አጠናክሮ በመተግበር ሠላማዊ የመማር ማስተማር ሂደትን ማስፈንና ማስቀጠል ነው፡፡

ከ2012 ትምህርት ዘመን ጀምሮ በዩኒቨርሲቲ ትምህርት 3 ዓመት የነበረው ዝቅተኛ የቅድመ ምረቃ ፕሮግራም 4 ዓመት የሚደረግ ሲሆን የሙያ ሥነ-ምግባር ኮርሶች በእያንዳንዱ የትምህርት መርሃ-ግብር ተካተው ይሰጣሉ፡፡ ተማሪዎች አገራቸውንና አካባቢያቸውን እንዲያውቁና እንዲረዱ፣ ለሙያ መስመር የሚያዘጋጁ ኮርሶችም የ21ኛውን ክ/ዘመን ክህሎት በሚያጠናክር ሁኔታ የ1ኛ ዓመት የትምህርት ፕሮግራም መቀየሱ ተገልጿል፡፡

የመምህራንና የቴክኒክ ረዳቶች ቅጥርና ስልጠና፣ የቤተ-ሙከራዎች ግብዓትና አደረጃጀት ማሻሻል፣ ዲጂታል ቤተ-መጽሐፍት አገልግሎት በማንኛውም ሥፍራ ለተገልጋይ ተደራሽ ማድረግ፣ ለመማር ማስተማር አስፈላጊ ግብዓቶችን ማሟላት፣ ካምፓሶችና ኮሌጆች ከማዕከል ጋር ተናበው ዕቅድ ማዘጋጀትና ተገቢውን ድጋፍ ማድረግ በዝግጅት ምዕራፍ ከተከናወኑ ተግባራት መካከል ናቸው፡፡

የኢንተርኔት መቆራረጥ፣ የቢሮና የኮምፒውተር እጥረት፣ በተማሪዎች አካባቢ የሚታይ የኃይማኖትና የብሔር ጽንፈኝነት፣ በካምፓሶች ዙሪያ የጫትና መሸታ ቤቶች መስፋፋት፣ መምህራን ለትምህርት ሲሄዱ ወጥ የሆነ አሠራር አለመኖር፣ የብቃት ማረጋገጫ ፈተና ተማሪዎችን በአግባቡ እየገመገመ አለመሆን እንዲሁም ዩኒቨርሲቲው በውኃ የልህቀት ማዕከል ለመሆን እየሠራ እንደመሆኑ የማኅበረሰቡን የንፁህ ውኃ ችግር ለመፍታት የሚያከናውናቸውን ሥራዎች አስመልክቶ ከተሳታፊዎች ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተዋል፡፡

በተጨማሪም የማኅበረሰብ አገልግሎት አገር በቀል እውቀቶች፣ መድኃኒቶች እና ባህላዊ እሴቶች ላይ በትኩረት እንዲሠራ፣ የሥነ-ምግባር ችግር ያለባቸው ሠራተኞች ላይ እርምጃ እንዲወሰድ፣ ችግር ፈቺ ምርምሮች የአስተዳደር ሠራተኞችንም እንዲያሳትፉ እንዲሁም ለአስተዳደር ሠራተኞች በየዓመቱ የሚሰጠው የ2ኛ ዲግሪ የትምህርት ዕድል ቁጥሩ ከፍ እንዲል አስተያየቶች ተሰጥተዋል፡፡

የመምህራን ልማት ስብጥር በተለይ የ3ኛ ዲግሪ መምህራን ቁጥር ለማሳደግ በትኩረት መሥራት፣ ከትምህርት ጥራትና መልካም አስተዳደር ጋር በተያያዘ ተማሪዎች፣ መምህራንና የአስተዳደር ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች ጋር በየጊዜው ውይይቶችን በማካሄድ ክፍተቶችን ማስተካከል፣ በተማሪዎች ንብረት ላይ የሚፈፀም ስርቆት፣ ቅሚያና አካላዊ ጥቃትን ማስቀረት እንዲሁም ሠላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲቀጥል ከተማሪዎች አደረጃጀት፣ ከአካባቢው አስተዳደርና ከማኅበረሰቡ ጋር ያለውን ትስስር ማጠናከር በቀጣይ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡

በለውጥ መሣሪያዎች በተለይ በካይዘንና ሚዛናዊ ውጤት ተኮር ሥርዓት የሥራ አፈፃፀም ምዘና ማከናወን፣ የምርምር ውጤቶችን ማላመድና ቴክኖሎጂዎችን ወደ ማኅበረሰብ ማሸጋገር፣ የገቢ ማመንጫ አማራጮችንና አሠራሮችን በማሻሻል ገቢ ማሳደግ፣ ነባር የግንባታ ፕሮጀክቶች እንዲጠናቀቁና አዲስ የተጀመሩ በውል መሠረት እንዲፈፀሙ መከታተል እና የግዥ ሥራ አፈፃፀምን ማቀላጠፍ በተጨማሪ የሚሠሩ ይሆናል፡፡

ከብዛት ወደ ጥራት፣ ከቅድመ ምረቃ ወደ ድኅረ-ምረቃ፣ ከትምህርት ተኮር ወደ ምርምርና ፈጠራ ተኮር፣ ከማኅበረሰብ አገልግሎት ወደ ማኅበረሰብ ተሳትፎና ተጠቃሚነት እና ከዘልማዳዊ የትምህርት አሰጣጥ ወደ ቴክኖሎጂ ተኮር መሸጋገር በ2012 ዓ.ም የተለዩ 5 አበይት የለውጥ ትኩረት አጀንዳዎች ናቸው፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት