ለአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ መካከለኛ አመራሮች የአመራርነት ሥልጠና ተሰጠ

ከኢትዮጵያ ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት በመጡ ባለሙያዎች ለዩኒቨርሲቲው መካከለኛ አመራሮች ከመስከረም 26-28/2012 ዓ/ም የአመራርነት አቅም ማጎልበቻ ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡

በፕሮግራሙ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ የአመራርነት ሥራ በአንድ ተቋም ውጤታማነት ላይ የአንበሳውን ድርሻ እንደሚወስድ ገልፀው መሪነት የራሱ ሣይንስ ያለው ተግባር በመሆኑ በአጫጭር የሥራ ላይ ሥልጠናዎች በመሳተፍ የአመራርነት ዕውቀትና ክህሎትን በተሻለ ደረጃ ታጥቆ መሥራት የሚጠበቀውን ውጤት ለማስመዝገብ እንዲሁም መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ጉልህ ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል፡፡ ምስሉን ለማየት ከዚህ ይጫኑ

የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር የቻለ ከበደ በበኩላቸው የዩኒቨርሲቲውን ራዕይና ተልዕኮ ዕውን ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ውስጥ የመካከለኛ አመራሩ ሚና የማይተካ በመሆኑ የአመራሩን አቅም ለማጎልበት ታስቦ ሥልጠናው እንደተዘጋጀ ገልፀዋል፡፡ ሥልጠናው የተሰጠባቸው ይዘቶች በዩኒቨርሲቲው በአመራር አሰጣጥ እንደ ክፍተት የታዩ ጉዳዮችን መሠረት ያደረጉ መሆናቸውን የተናገሩት ዶ/ር የቻለ ሥልጠናው የአመራርነት ክፍተቶችን በመሙላት የዩኒቨርሲቲው አጠቃላይ ሥራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ ያግዛል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት አቶ ተረፈ ትዜ ተቋማቸው የመንግሥትም ሆነ የግል ተቋማት ቀልጣፋና ውጤታማ አገልግሎት መስጠት አንዲችሉ በዘመናዊ ሥራ አመራር ልማት መስክ የሥልጠና፣ የምክርና የምርምር አገልግሎት እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡ ሥልጠናው የዩኒቨርሲቲውን ጥያቄ መሠረት በማድረግ እንደተዘጋጀና በዋናነት በአመራርነት ዙሪያ የሚስተዋሉ የክህሎት ክፍተቶችን መሙላት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡

ከሠልጣኞች መካከል የግብርና ሣይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ይስሀቅ ከቸሮ ከሥልጠናው በርካታ አዳዲስ ግንዛቤዎችን እንዳገኙ ገልፀው ብቁ ዜጋ ለማፍራት፣ በምርምርም ሆነ በማኅበረሰብ አገልግሎት መስክ ውጤታማ ለመሆን እንዲሁም የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ ሥልጠናው አጋዥ ነው ብለዋል፡፡

ሌላኛዋ ሠልጣኝ የኢኮኖሚክስ ት/ክፍል ኃላፊ ወ/ሮ አምሳለ ተክሌ በበኩላቸው ሥልጠናው ከዚህ ቀደም በተለምዶ የሚሠሯቸውን ሥራዎች በማስቀረት አፈፃፀማቸውን ለማሻሻል እንደሚያግዝ ገልፀው በአገልግሎት አሰጣጥ፣ በሠራተኞች አያያዝና አሠራርን ከማሻሻል አንፃር ከሥልጠናው ጥሩ ግንዛቤ እንዳገኙ ተናግረዋል፡፡

በሥልጠናው የኮሌጅና ት/ቤት ዲኖች፣ የትምህርት ክፍል ኃላፊዎች፣ የሥራ ክፍል ዳይሬክተሮችና አስተባባሪዎች ተሳትፈዋል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት