አቶ ገ/መድኅን ጫሜኖ በምክትል ፕሬዝደንት ማዕረግ የሳውላ ካምፓስ ኃላፊ ሆነው ተሾሙ

የሳውላ ካምፓስ ዲን የነበሩት አቶ ገ/መድኅን ጫሜኖ በምክትል ፕሬዝደንት ማዕረግ የሳውላ ካምፓስ ኃላፊ ሆነው በዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ቦርድ ተሹመዋል፡፡ በአዲሱ መዋቅር መሠረት ካምፓሱ የአካዳሚክና አስተዳደር ጉዳዮች ዳይሬክተሮች ይኖሩታል፡፡

በቀድሞው ጋሞ ጎፋ ክፍለ-አገር በጎፋ አውራጃ ሎጤ ጋይላ ጫልቤ ቀበሌ የተወለዱት አቶ ገ/መድኅን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በሎጤ ሙሉ 1ኛ ደረጃ ት/ቤት እንዲሁም የ2ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በሳውላ 2ኛ ደረጃና መሰናዶ ት/ቤት ተከታትለዋል፡፡ አቶ ገ/መድኅን የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ በዕጽዋት ሣይንስ ያገኙ ሲሆን የ2ኛ ዲግሪያቸውን ከሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ በጥምር ግብርና መስክ አግኝተዋል፡፡

አቶ ገ/መድኅን በጎፋ ዙሪያ ወረዳ የምግብ ዋስትና ፕሮጀክት አስተባባሪና የግብርናና ገጠር ልማት ጽ/ቤት ምክትል ኃላፊ፣ የዴንባ ጎፋ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ እንዲሁም የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ በመሆን አገልግለዋል፡፡ በተጨማሪም በጋሞ ጎፋ ዞን የግብርና መምሪያ ኃላፊና የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪ በመሆን እንዲሁም የዞኑ ግብይትና ኅብረት ሥራ መምሪያ ኃላፊ ሆነው አስከ 2007 ዓ/ም ድረስ ሕዝብና መንግሥት የጣለባቸውን ኃላፊነት ሲወጡ ቆይተዋል፡፡ በ2007 ዓ/ም ዩኒቨርሲቲውን በመምህርነት የተቀላቀሉት አቶ ገ/መድህን ከመስከረም 2008 ዓ/ም ጀምሮ የሳውላ ካምፓስ ዲን በመሆን አገልግለዋል፡፡

አቶ ገ/መድኅን አዲሱን የካምፓስ መዋቅር አስመልክቶ በሰጡት አስተያየት መዋቅሩ የማስፈጸም አቅምንና ውሳኔ ሰጪነትን በማጎልበት ለካምፓሱ ዕድገትና ውጤታማነት ጉልህ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡ ካምፓሱ አዲስ እንደመሆኑና ከማዕከል ካለው ርቀት አንጻር በርከት ያሉ የመልካም አስተደደር ችግሮችና ጥያቄዎች እንደሚነሱ የተናገሩት አቶ ገ/መድኅን መዋቅሩ መሰል ጥያቄዎች ለመመለስ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ድርሻው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ይህ መዋቅር በካምፓሱ እንዲፈጠር ከፍተኛ ጥረት ሲደረግ እንደነበር የተናገሩት አቶ ገ/መድኅን የጥያቄውን ተገቢነትና አስፈላጊነት በመረዳት መዋቅሩ ተግባራዊ እንዲሆን ላደረጉት ለዩኒቨርሲቲው አመራሮችና የአስተዳደር ቦርድ አባላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

በ2012 የትምህርት ዘመን በተማሪዎች የሚነሱ የትምህርት ጥራትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ በትኩረት እንደሚሠሩ የተናገሩት ኃላፊው ከመማር ማስተማር ሥራ ባሻገር የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ሥራዎችም ትኩረት እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል፡፡

አቶ ገ/መድኅን የ2012 የትምህርት ዘመን ሠላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ሲከናወኑ እንደነበር ተናግረው በዚህም ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮችን በመለየት ከዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ጋር ውይይቶች ተደርገዋል ብለዋል፡፡ የአካባቢው ማኅበረሰብ ካምፓሱን እንደ ዓይኑ ብሌን ይመለከተዋል ያሉት አቶ ገ/መድህን ከጎፋ ዞንና ከሳውላ ከተማ አስተዳደር ጋር በጋራ እንደሚሠሩም ገልፀዋል፡፡

ሳውላ ካምፓስ 6ኛው የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ካምፓስ በመሆን በ2008 ዓ/ም ማስተማር የጀመረ ሲሆን በተለያዩ ፕሮግራሞች ለሁለት ዙር ተማሪዎችን ማስመረቁ ይታወሳል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት