ለተማሪዎች አገልግሎት ሠራተኞች የተግባቦት ስልጠና ተሰጠ

የስነ-ትምህርትና ስነ-ባህርይ ሣይንስ ት/ቤት ለዋናው ግቢና ጫሞ ካምፓሰ የተማሪዎች አገልግሎት ሠራተኞች ከመስከረም 19-20/2012 ዓ/ም ከተማሪዎች ጋር የተሻለ ተግባቦት ለመፍጠር የሚያስችል ስልጠና ሰጥቷል፡፡ ምስሉን ለማየት ከዚህ ይጫኑ

የስነ-ትምህርትና ስነ-ባህርይ ሣይንስ ት/ቤት ዲን አቶ አንለይ ብርሃኑ እንደገለጹት ስልጠናው ሠራተኞች እርስ በእርስና ከተማሪዎች ጋር የተሻለ ተግባቦት መፍጠር እንዲችሉ በተግባቦትና የተግባቦት እንቅፋቶች ዙሪያ ትኩረት ያደረገ ነው፡፡ ስልጠናው በዓመቱ መጀመሪያ መሰጠቱ ከተግባቦት ክህሎት ማነስ የተነሳ የሚፈጠር አላስፈላጊ ግጭት በመቀነሰ በሠራተኞች መካከልና በሥራ አካባቢ ጤናማ ግንኙነት እንዲኖር የሚያስችል መሆኑን አቶ አንለይ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በሁለቱ ካምፓሶች ሠራተኞችና ተማሪዎች በሚያደርጉት ግንኙነት የተስተዋሉ ያለመግባባት ችግሮች በያዝነው የትምህርት ዘመን እንዳይከሰቱ፣ ተማሪዎች ተገቢውን አገልግሎት እንዲያገኙና ሠራተኞችም ደስተኛ ሆነው እንዲሠሩ ስልጠናው ለዋና ግቢና ጫሞ ካምፓሰ የተማሪዎች አገልግሎት ሠራተኞች የተሰጠ መሆኑን ዲኑ ገልጸዋል፡፡ ሠልጣኞቹ ያገኙትን ክህሎት ወደ ተግባር በመቀየር የሚያሳዩትን ለውጥ በመመልከት በቀጣይ ለሁሉም ካምፓስ ሠራተኞች ለመስጠት አቅደናልም ብለዋል፡፡

በመኝታ አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ የፍራሸ፣ ትራስ፣ ወንበር፣ የበር ቁልፍ፣ የፊት መስታዎት ወዘተ ቁሳቁሶች በጊዜ አለመቅረብ አለመግባባትን የሚፈጥር ሲሆን አዲስ ገቢ ተማሪዎች ቤተ-መጽሐፍት ሲገለገሉ የመጽሐፉን ደራሲ ስም፣ ይዘት፣ የህትመት ዘመንና የአሳታሚ ድርጅት የመሳሰሉትን ትተው የመጽሐፉን ርዕስ ብቻ ይዘው በመምጣት ከቤተ- መጽሐፍት ሠራተኞች ጋር የሚፈጥሩት ግብግብ እንደ ችግር ተነስቷል፡፡ ተማሪዎቹ ለዩኒቨርሲቲው እንግዳ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ መሰል ክስተቶች ሲፈጠሩ ሠራተኞች በቅንነትና በአገልጋይነት መንፈስ እንዲያስተናግዱ እንዲሁም የደኅንነት ሠራተኞች ከተማሪዎች ጋር መልካም ግንኙነት እንዲኖራቸውና አልፎ አልፎ የሚከሰቱ ግጭቶችን በውይይትና በሠላማዊ መንገድ መፍታት እንዲችሉ በስልጠናው ግንዛቤ ተፈጥሯል፡፡

የመኝታ አገልግሎት፣ የመስተንግዶ፣ የቤተ-መጽሐፍት እና የደኅንነት ሠራተኞች ስልጠናውን የተካፈሉ ሲሆን በተለይ አዲስ ለተቀጠሩና በJEG ተመድበው ወደ ተማሪዎች አገልግሎት ለተቀላቀሉ ሠራተኞች መሰጠቱ ጠቃሚ መሆኑን ተሳታፊዎች አስተያየት ሰጥተዋል፡፡