ዩኒቨርሲቲው የበቆሎ መፈልፈያ መሳሪያ አዘጋጅቶ ለ3 ወረዳዎች ለሙከራ አቀረበ

ዩኒቨርሲቲው በጋሞ ዞን ውስጥ ከሚገኙ 3 ከፍተኛ የበቆሎ አምራች ወረዳዎች የመጡ ሞዴል አርሶ አደሮች በተገኙበት ጥቅምት 4 እና 5 የበቆሎ መፈልፈያ መሣሪያ ለሙከራ አቅርቧል፡፡

ከምዕራብ አባያ 3 ቀበሌያት 20፣ ከቁጫ 10 ቀበሌያት 20 እና ከዳራማሎ 7 ቀበሌያት 40 ሞዴል አርሶ አደሮች ተገኝተው የመፈልፈያውን አጠቃቀም እንዲለምዱና ለሌሎች እንዲያሸጋግሩ በአያያዙና አጠቃቀሙ ዙሪያ በዘርፉ ባለሙያ ገለጻ ተደርጓል፡፡ ምስሉን ለማየት ከዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲ ኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ቶሌራ ሴዳ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው የህብረተሰቡን ችግር ለመፍታት በምርምር ያገኛቸውን ግኝቶች ከኢንደስትሪዎች ጋር በማዋሃድ አዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ለህብረተሰቡ ለማድረስ ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል የቴክኖሎጂ ሽግግር አንዱ ነው፡፡ የበቆሎ መፈልፈያ መሣሪያውን ለህብረተሰቡ በማስተዋወቅ ውጤታማ መሆኑ ተረጋግጦ ለሌሎች እንዲዳረስ የሚደረግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በበኩላቸው የበቆሎ መፈልፈያ መሣሪያው የአርሶ አደሩን ችግር በማቅለል ምርቱ እንዲጨምርና የህብረተሰቡ ኑሮ እንዲሻሻል ያግዛል ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ከዚህ ቀደም ዘመናዊ የወተት መናጫ ቴክኖሎጂን ሳውላና ካምባ አካባቢ ለሚገኙ አርሶ አደሮች ማቅረቡንም አስታውሰዋል፡፡

የሲቴክ ስሪ ዲ ፕሪንትና ዘመናዊ የፈርኒቸር ሥራ ማኅበር ሰብሳቢ አቶ ሐብታሙ ላቀው የቴክኖሎጂ ውጤቱ በመጠን ትንሽ ቢሆንም ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ያደጉ የአፍሪካና የአውሮፓ አገራት ውጤታማነቱን በመረዳት በከፍተኛ ሁኔታ እየተጠቀሙበት ይገኛልም ብለዋል፡፡

የበቆሎ መፈልፈያው በ1 ደቂቃ 2 ኪሎ የሚፈለፍል ሲሆን አርሶ አደሮች ከዚህ ቀደም በእጅ ለመፈልፈል የሚያጠፉትን ጊዜና ጉልበት የሚቀንስ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ መሣሪያው የእጅ ጣትን ለጉዳት የማይዳርግ፣ የበቆሎን የዘር ፍሬ የማይሰብር፣ ጊዜን የሚቆጥብ፣ የኤሌትሪክ ኃይል የማይፈልግ፣ ለአጠቃቀም ቀላልና ጥገና የማይፈልግ መሆኑ የቴክኖሎጂውን ውጤታማነት እንደሚያረጋግጥ አቶ ሐብታሙ አብራርተዋል፡፡

የአርሶ አደሮችን ጭንቀት ለመቀነስና ከዚህ ቀደም ሲጠቀሙ የነበረውን የመፈልፈያ ዘዴ ለመቀየር ለረጅም ጊዜ ጥናት ሲያደርጉ መቆየታቸውን አውስተው ይህን የመፈልፈያ መሣሪያ ለመፍጠር የማላዊ፣ ታንዛኒያና ደቡብ አፍሪካን ተሞክሮ መመልከታቸውንና ከዩኒቨርሲቲው ጋር አብረው ለመሥራት መነሳሳታቸውን ጠቁመዋል፡፡

ከምዕራብ አባያ ወረዳ ቆላ ሙላቶ ቀበሌ የመጣው ሞዴል አርሶ አደር ታደሠ ግርማ በሰጠው አስተያየት ቴክኖሎጂው ጉልበት ቆጣቢና የበቆሎውን ፍሬ የማይሰብር በመሆኑ ምርቱ ወደ ገበያ ሲቀርብ የተሻለ ዋጋ እንደሚያስገኝለት ተናግሯል፡፡

ከዚህ ቀደም አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ስለግብርና ምርቶች አያያዝና አጠባበቅ ብዙ ትምህርቶችን መስጠቱን የገለጸው ከቁጫ ወረዳ ጋሌ ቀበሌ የመጣው አርሶ አደር አብርሃም አንጃ በበኩሉ ቴክኖሎጂው በጥቂት ጊዜ ውስጥ ብዙ መፈልፈል የሚያስችልና ለምርት ጥራት ተስማሚ በመሆኑ በቀጣይ ወደ ሌሎች አርሶ አደሮችም ማውረድ እንደሚያስፈልግ ተናግሯል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት