የዩኒቨርሲቲ ኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ከአርባ ምንጭ ፖሊ ቴክኒክና ሳተላይት ኢንስቲትዩት ጋር በጋራ በመሆን በዩኒቨርሲቲው ክላስተር ስር ካሉ 13 የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ለተወጣጡ 63 የቴክኒክና ሙያ መ/ራን ከጥቅምት 3 – 10/2012 ዓ/ም ድረስ የሶፍትዌር ክህሎት ማሻሻያ የአሰልጣኞች ስልጠና ሰጥቷል፡፡ መምህራኑ ወደ መጡበት ሲመለሱ ስልጠናውን ላልወሰዱት ተደራሽ የሚያደርጉ ይሆናል፡፡ ምስሉን ለማየት ከዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲ ኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ቶሌራ ሴዳ እንደገለፁት ስልጠናው በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎችን አቅም በመገንባት ከስልጠናው ያገኙትን ክህሎት ወደ ተግባር በመለወጥ የተሻሉ ቴክኖሎጂዎችን ማምረት ያስችላል፡፡

ተማሪዎች በክፍል ውስጥ የተማሩትን ወደ ተግባር ለውጠው የሚታዩና የሚጨበጡ ቴክኖሎጂዎችን እንዲሠሩ ለማድረግ ስልጠናው ወሳኝ ነው ያሉት የዩኒቨርሲቲ ኢንደስትሪ ትስስር ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ ዶ/ር ሽታዬ ጋተው መምህራን ለተማሪዎቻቸው የተሻሉ ቴክኖሎጂዎችን በማስተላለፍ፣ በተግባር ሠርተው እና አዳብረው ከዘመኑ ጋር አብረው የሚሄዱ ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎችን ይሠራሉ ተብሎ ይገመታል ብለዋል፡፡

የሥነ-ህንፃና ከተማ ፕላን ፋከልቲ ረዳት መ/ር አሪሬ ገመዴ የአርኪ-ካድ /Archi Cad/ ሶፍትዌር ላይ ስልጠና የሰጡ ሲሆን ሶፍትዌሩ በሁለት አቅጣጫ /2D/ ብቻ ተወስነው የተዘጋጁ የግንባታ ንድፎችን ወይም የቤት ካርታዎችን ወደ ሦስት አቅጣጫ /3D/ ወዳሉት ተቀይሮ ሲገነባ በአጠቃላይ ህንፃው ምን ሊመስል እንደሚችል የሚያሳዩበት ከመሆኑም ባሻገር የአርክቴክቸር ዲዛይን በትክክል ነድፈው ግንባታዎችን መሥራት እንዲችሉ የሚረዳ ነው ብለዋል፡፡

ከአርባ ምንጭ ፖሊ ቴክኒክና ሳተላይት ኢንስቲትዩት መ/ር ኤርሚያስ ድጉማ በልብስ ዲዛይን መስሪያ ሶፍትዌር ላይ ስልጠና የሰጡ ሲሆን ሶፍትዌሩ የተለያዩ ልኬቶችን ከሰዎች በመውሰድና በኮምፒውተር በመታገዝ ለለባሹ የሚመጥን ልብስ ለማምረት የሚጠቅም መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ሰልጣኞች ወደ ኢንደስትሪው ሄደው ግብዓቱን በተግባር በማሳየት ለኢንደስትሪው ድጋፍ እንዲሰጡ የሚያስችል ከመሆኑም ባሻገር የኢንደስትሪ ሥራ ከሰዓት ጋር የተያያዘ በመሆኑ በአጭር ጊዜ አምርተው ትርፋማነታቸው እንዲጨምር የሚረዳ፣ ሥራን የሚያቃልል እና የጨርቅ ብክነት እንዳይኖር የሚያደርግ ሶፍትዌር መሆኑን አክለዋል፡፡ ይህንንም ወደ ተማሪዎቻችን በማውረድ ወደ ኢንደስትሪው ተቀላቅለው አገራቸውንም ሆነ ራሳቸውን መጥቀምና ኢንደስትሪውን ውጤታማ በማድረግ አገሪቷን በዘርፉ ተወዳዳሪ ማድረግ እንዲችሉ ማብቃት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ሌላኛው አሰልጣኝ ከሜካኒካል ኢንጂነሪንግ ፋከልቲ መ/ር አዳነ ካሳ በ ‹Solid Work› ሶፍትዌር ላይ ያተኮረ ስልጠና የሰጡ ሲሆን በብረታ ብረትና በእንጨት ሥራዎች ለተደራጁ ማኅበራት የሚፈልጉትን ምርት በተለያዩ ዲዛይኖች መቅረፅ የሚያስችልና የሚሠሩትን ሥራ በትክክል መግጠም እንዲችሉ የሚረዳ ሶፍትዌር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ፖሊ ቴክኒክና ሳተላይት ኢንስቲትዩት ም/ዲን እና የቴክኖሎጂ ሽግግርና ኢንደስትሪ ኤክስቴንሽን ዋና የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ወርቅነህ ኃ/ሚካኤል ስልጠናው የአሰልጣኞች ስልጠና እንደመሆኑ መጠን በሰለጠኑት ልክ በተግባር ልምምዱን ሠርተው ሲሄዱ ሌሎችንም የማብቃት ሥራ ሊሠሩ ይገባል ብለዋል፡፡

ሰልጣኞች በሰጡት አስተያየት ሶፍትዌር በየጊዜው እየተሻሻለ ስለሚመጣ እራሳቸውን ከአዲሱ ሶፍትዌር አጠቃቀም ጋር ማስተዋወቅ ወደፊት ለሚሠሯቸው ሥራዎች የሚረዳ መሆኑን ተናግረው በአንዳንድ አካባቢዎች የኢንተርኔት ዕድል ባለመኖሩ ያሰቡትን ያህል ለመንቀሳቀስ እንቅፋት ሊሆንባቸው እንደሚችል ስጋታቸውን ገልፀዋል፡፡ በተጨማሪም አሰልጣኞቹንና አዘጋጆቹን አመስግነው በቀጣይ በተለያዩ ሶፍትዌሮች ላይ ስልጠናው እንዲቀጥልም ጠይቀዋል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት