የዩኒቨርሲቲው ሴኔት ሐምሌ 3/2011 ዓ/ም ባካሄደው ውይይት ለደረጃው ካመለከቱ መምህራን መካከል መስፈርቱን ላሟሉ 3 ነባር መምህራን የተባባሪ ፕሮፈሰርነት ማዕረግ የሰጠ ሲሆን በተመሳሳይም ጥቅምት 20/2012 ዓ/ም በተደረገው ውይይት 4 ነባር መምህራን የተባባሪ ፕሮፈሰርነት ማዕረግ እንዲያገኙ ሴኔቱ ወስኗል፡፡

ከኅብረተሰብ ጤና ሣይንስ ት/ክፍል አቶ በኃይሉ መርደክዮስ፣ ከስፖርት ሣይንስ ት/ክፍል ዶ/ር ሞላ ዶዮ እና ከእንግሊዝኛ ት/ክፍል ዶ/ር አባተ ደምስ ሐምሌ 3/2011 ዓ/ም ሴኔቱ ባካሄደው ውይይት ማዕረጉን ያገኙ ሲሆን ሴኔቱ ጥቅምት 20/2012 ዓ/ም ባካሄደው ውይይት ከተፈጥሮ ሣይንስ ኮሌጅ ዶ/ር ፍቃዱ ማሴቦ፣ ዶ/ር አለማየሁ ኃ/ሚካኤልና ዶ/ር ራሚሽ ዱረሰሚ እንዲሁም ከማኅበራዊ ሣይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ ከጂኦግራፊና አካባቢያዊ ጥናት ትምህርት ክፍል ዶ/ር የቻለ ከበደ የተባባሪ ፕሮፈሰርነት ማዕረግ እንዲያገኙ አጽድቋል፡፡

መምህራኑ በውጤታማ የማስተማር ተግባር፣ ሣይንሳዊ የምርምር ውጤቶችን ዓለም አቀፍ ዕውቅና ባላቸው ጆርናሎች ላይ ለኅትመት በማብቃት እና በተለያዩ የማኅበረሰብ አገልግሎት ተሳትፎዎች በሴኔቱ መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 8 የተቀመጡ መስፈርቶችን በማሟላት ለማዕረጉ ብቁ ሆነው በመገኘታቸው የዩኒቨርሲቲው ሴኔት ተወያይቶ የማዕረግ እድገት እንዲሰጣቸው ወስኗል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የሴኔት መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 8 በሚያዘው አሠራር መሠረት በረዳት ፕሮፈሰርነት ማዕረግ 4 ዓመት ውጤታማ የማስተማር ተግባር ያከናወነ፣ ቢያንስ 2 አርቲክሎችን በታዋቂ ጆርናሎች ላይ ያሳተመ፣ በቀዳሚ ምርምር ሥራው ላይ መጽሐፍ ያዘጋጀ ወይም አራት የምርምር ፕሮጀክቶችን የቀረጸና አንድ አርቲክል ያሳተመ ወይም ሁለት ፕሮጀክት የቀረጸ፣ አንድ አርቲክል ያሳተመና አንድ ቴክኖሎጂ ያሸጋገረ መምህር ለማዕረግ እድገቱ መወዳደር እንደሚችል ተጠቅሷል፡፡

በተመሳሳይ ለዚህ የማዕረግ ደረጃ አመልካቹ በዩኒቨርሲቲው ጉዳዮች ላይ ንቁ ተሳትፎ ያደረገና በአዲሱ የሣይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር መመሪያ መሠረት የማኅበረሰብ አገልግሎት ዘርፍን እንደ አንድ የመማር ማስተማር አካል አድርጎ በማኅበረሰብ አገልግሎት ሥራዎች ላይ አስተዋጽኦ ያበረከተ ተወዳዳሪ ብቁ መሆን እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት