ከኤልጎ ተፋሰስ ብቻ በየዓመቱ 3.3 ሚሊየን ቶን ደለል አፈር ወደ ጫሞ ሐይቅ እንደሚገባ በጥናት ተረጋገጠ

የጫሞ ሐይቅ ዋነኛ ተፋሰስ በሆነው የኤልጎ ተፋሰስ ላይ የአፈር መሸርሸር መጠንን ለማወቅ ሲከናወን የነበረው የምርምር ፕሮጀክት ውጤት ይፋ ሆኗል፡፡ በጥናቱ መሠረት ከኤልጎ ተፋሰስ ብቻ በየዓመቱ 3.3 ሚሊየን ቶን ደለል አፈር እየተሸረሸረ ወደ ጫሞ ሐይቅ እንደሚገባ ተረጋግጧል፡፡ የደለል መጠኑ ሌሎች የሐይቁ ዋነኛ ተፋሰስ የሆኑትን ኩልፎና ሲሌ ተፋሰሶችን አያካትትም፡፡ ምስሉን ለማየት ከዚህ ይጫኑ

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የAMU-IUC ፕሮግራም ኃላፊና የውኃ ሥነ-ምኅዳር ተመራማሪው ዶ/ር ፋሲል እሸቱ እንደገለፁት የምርምር ፕሮጀከቱ በዋናነት ሐይቁን ለመታደግ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ሐይቁን ከተፋሰሱ ለይቶ ማየት እንደማይቻል በመታመኑና ተፋሰሱ ለይ ትኩረት አድርጎ መሥራቱ ሐይቁን ለማዳን ጉልህ ሚና እንዳለው በመታመኑ የምርምር ፕሮጀክቱን ለመሥራት አነሳስቷል፡፡

የጫሞ ሐይቅ ያሉት ተፋሰሶች በአጠቃላይ 1,495 ስኩዌር ኪሎ ሜትር እንደሚሸፍኑ የተናገሩት ዶ/ር ፋሲል ከዚህም ውስጥ የኤልጎ ተፋሰስ 285 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ቦታን ይሸፍናል፡፡ በተደረገው ጥናትም ከዚሁ ተፋሰስ ብቻ 3.3 ሚሊየን ቶን ደለል አፈር በየዓመቱ ከተፋሰሱ ተጠርጎ ወደ ጫሞ ሐይቅ እንደሚገባ መረጋገጡን ተመራማሪው ገልፀዋል፡፡ ይህ ቁጥር ብቻውን አስደንጋጭ እንደሆነ የሚናገሩት ዶ/ር ፋሲል ከኩልፎ፣ ሲሌና ሌሎች ተፋሰሶች የሚገባው የደለል መጠን ሲጨመር የሐይቁ ሕልውና ምን ያህል አደጋ ውስጥ እንዳለ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

የአፈር መሸርሸርን ለማጥናትና ምን ያህል አፈር በየጊዜው እንደሚሸረሸር ለማወቅ የተፋሰሱ የአፈር ተፈጥሮና ዓይነት፣ የዝናብ ስርጭት፣ የመሬቱ ተዳፋትነት፣ የዕፅዋት ወይም የደን ሽፋን እና የአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራዎች አተገባበርን ማጥናት አስፈላጊ በመሆኑ እነዚህ 5ቱ ምክንያቶች የስሌቱ አካል በመሆን የመጨረሻ ውጤቱ ላይ ለመድረስ ማስቻላቸውን ዶ/ር ፋሲል ተናግረዋል፡፡

በአካባቢው በአጭር ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ የሚዘንብ መሆኑ በጥናቱ መረጋገጡን የሚናገሩት ዶ/ር ፋሲል ይህም መሬቱ በከፍተኛ ሁኔታ በመታረሱና የአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራ ባለመሠራቱ እንዲሁም ከአፈሩ ተፈጥሮ ጋር ተዳምሮ አፈሩ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲሸረሸር ከፍተኛ ሚና ይጫወታል ብለዋል፡፡

ከተፋሰሱ የመሬት ክፍል 80 በመቶው ለእርሻ የዋለ ሲሆን ለአፈር መሸርሸሩ 63 በመቶ ድርሻ የሚያበረክተው ግብርናው መሆኑ በጥናቱ መረጋገጡን ተመራማሪው ገልጸዋል፡፡ የመሬቱ ተዳፋትነት ለአፈር መሸርሸሩ የራሱ ድርሻ አለው ያሉት ዶ/ር ፋሲል በመንግሥት ፖሊሲ ደረጃ የተዳፋትነት ደረጃው 30 በመቶ የሆነ መሬት እንዲታረስ ባይፈቀድም በአካባቢው ከ60-70 በመቶ የተዳፋትነት ደረጃ ያለቸው ቦታዎች ጭምር መታረሳቸው ለአፈር መሸርሸሩ ትልቅ ሚና አበርክተዋል ብለዋል፡፡

በሐይቁ ዙሪያ ያለው ረግረጋማ ቦታ መጥፋቱና መታረሱ ከተፋሰሱ የሚመጣው ደለል በቀጥታ ወደ ሐይቁ እንዲገባ ያደርገዋል ያሉት ዶ/ር ፋሲል ይህንንም ቦታ ከዚህ ቀደም ወደ ነበረበት ቦታ መመለስና እንደ ደንገል፣ ፊላና ሶኬ ባሉ የረግረጋማ አካባቢ ዕፅዋት መሸፈን ይገባል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ወደ ሐይቁ በከፍተኛ ሁኔታ የሚገባው ደለል የሐይቁን የምግብ ሰንሰለት ሥርዓት በማዛባት በሐይቁ ውስጥ በሚገኘው ብዝሃ ሕይወት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ነው ያሉት ዶ/ር ፋሲል የሐይቁ ዓሳ ሐብት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተመናመነ መምጣቱ የዚሁ ችግር ማሳያ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ከምርምር ሥራው ባሻገር በተፋሰሱና በሐይቁ ዙሪያ የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል ያሉት ተመራማሪው የኤልጎ ተፋሰስ የሆነውን የጌዣ ደንን ከመንከባከብ ባሻገር በዚሁ ደን ክልል ውስጥ 17 ሄክታር ቦታ ላይ ከ GIZ ጋር በመተባበር ዛፎች ተተክለው እንክብካቤ እየተደረገላቸው መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በተለያዩ አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ የምርምር ዓውደ ጥናቶች ላይ ይህ የምርምር ሥራ እየቀረበ መሆኑን የተናገሩት ዶ/ር ፋሲል በዚህም ምክንያት የተለያዩ በተፈጥሮ ጥበቃ ላይ የሚሠሩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጫሞ ሐይቅን ለማዳን በሚደረገው ጥረት ውስጥ የበኩላቸውን ለመወጣት ፍላጎት አሳይተዋል ብለዋል፡፡ ይህም በቅርቡ እውን እንደሚሆን ተስፋ እንደሚያደርጉ ዶ/ር ፋሲል ገልፀዋል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት