ዩኒቨርሲቲው ለሠላም በር ኮንስትራክሽንና ኢንደስትሪያል ኮሌጅ የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ

የሠላም በር ኮንስትራክሽንና ኢንደስትሪያል ኮሌጅ ለትምህርት ግብዓት የሚሆን የቁሳቁስ ድጋፍ እንዲደረግለት በጠየቀው መሠረት ጥቅምት 28/2012 ዓ/ም ዩኒቨርሲቲው ሦስት መቶ ሃምሳ ሺህ ብር የሚገመት የኮምፒዩተር፣ የጥቁር ሠሌዳና የወንበር ድጋፍ አድርጓል፡፡Click here to see the pictures
የማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ ድጋፉ በዋናነት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የሚረዳ መሆኑን ተናግረው ኮሌጁ ቁሳቁሶቹን ኃላፊነት በተሞላው መልኩና በአግባቡ መጠቀም እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ከዚህ ቀደም ለበርካታ ትምህርት ቤቶችና የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች የሶፍትዌርና የICT ስልጠናዎችና የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግ ያወሱት ዳይሬክተሩ በተለያዩ ስልጠናዎችና ልምድ ልውውጦች አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲ ኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ቶሌራ ሴዳ በበኩላቸው ኮሌጁ የድጋፍ ጥሪ ሲያደርግ በኮሌጁ በአካል በመገኘት የመማሪያ ቁሳቁሶች እጥረት መኖሩን በመታዘባችን ድጋፉን አድርገናል ብለዋል፡፡ ኮሌጁ ጥራት ያለው ትምህርት በመስጠት ሥራ ፈጣሪ፣ ችግር ፈቺ እና ለአገርና ለቤተሰብ ኃላፊነት የሚሰማው ትውልድ  እንዲያፈራ ድጋፉ አስተዋፅኦ እንደሚኖረውም ተናግረዋል፡፡
የሠላም በር ኮንስትራክሽንና ኢንደስትሪያል ኮሌጅ ዲን አቶ ዳርዛ ደምሴ ኮሌጁ የሚሰጠውን ስልጠና በጥራት አጠናክሮ እንዳይቀጥል የግብዓት ችግሮች እንደነበሩበት ገልጸው ዩኒቨርሲቲው ያደረገው ድጋፍ በተለይ የኮምፒዩተር ድጋፉ የመማር ማስተማር ሥራውን ለማዘመን ይረዳል ብለዋል፡፡
ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት