ዩኒቨርሲቲው ለቁጫ ወረዳ ሴት ሞዴል አርሶ አደሮች ዘመናዊ የወተት መናጫ ቴክኖሎጂ አሸጋገረ

ዩኒቨርሲቲው በቁጫ ወረዳ ከፍተኛ የወተት አምራች ከሆኑ 3 ቀበሌያት ለተወጣጡ 18 ሴት ሞዴል አርሶ አደሮች ጥቅምት 29/2012 ዓ/ም ዘመናዊ የወተት መናጫ አጠቃቀም ስልጠና በመስጠት ቴክኖሎጂውን አሽጋግሯል፡፡Click here to see the pictures
የዩኒቨርሲቲ ኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሸግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ቶሌራ ሴዳ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው የማኅበረሰቡን ችግር ለመፍታት የምርምር ግኝቶችን ከኢንደስትሪዎች ጋር በማዋሃድ አዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ለኅብረተሰቡ እያሸጋገረ ይገኛል፡፡ ይህ ዘመናዊ የወተት መናጫ መሣሪያ ከሞርካ፣ ኩሎና ውዘቴ ቀበሌያት ለተወጣጡ ሴት ሞዴል አርሶ አደሮች ለሙከራ የቀረበ ሲሆን በአጠቃቀም ስልጠና የተሳተፉ ሰልጣኞች በሚሰጡት ግብረ መልስ ላይ ተመርኩዞ በቀጣይ በስፋት ለማሰራጨት ዩኒቨርሲቲው ዝግጁ መሆኑን ዶ/ር ቶሌራ ተናግረዋል፡፡
የማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው የተለያዩ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለሙከራ አቅርቦ ተጠቃሚዎች በሚያቀርቡት ግብረ መልስ መሠረት አኩሪ ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል፡፡ ሞዴል አርሶ አደሮቹ የወተት መናጫ አጠቃቀም ስልጠናውን ወደ ተግባር በመቀየር ለሌሎች ምሣሌ እንዲሆኑ  ዶ/ር ተክሉ አስገንዝበዋል፡፡
የቁጫ ወረዳ የእንስሳትና እጽዋት ዘርፍ ጽ/ቤት ተወካይ ዶ/ር አብርሃም ዘክዮስ እንደተናገሩት ከዚህ በፊት በወረዳው ሴቶች በባህላዊ መንገድ ወተት በሚንጡበት ወቅት ከ1፡00 - 1፡30 ሰዓት የሚሆን ጊዜ የሚወስድ ሲሆን ዘመናዊ የወተት መናጫው ከ8-10 ደቂቃ ውስጥ ቅቤ የሚያወጣ በመሆኑ የኅብረተሰቡን ችግር በተጨባጭ የሚፈታ ቴክኖሎጂ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲው የኅብረተሰቡን ችግር የሚፈቱ የምርምር ውጤቶችን ማቅረቡ የሚደነቅ ተግባር ነውም ብለዋል፡፡  
ሴት ሞዴል አርሶ አደሮቹ ቴክኖሎጂው ጊዜ ቆጣቢ፣ የሥራ ጫና የሚቀንስ፣ በጥሩ ሁኔታ ቅቤ እንዲወጣ የሚያግዝና ከዚህ ቀደም ከሚጠቀሙት ልማዳዊ አሠራር የተሻለ መሆኑን ጠቅሰው ቴክኖሎጂውን በስፋት ገበያ ላይ ለማዋል ዩኒቨርሲቲው እንዲሠራ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት