ዩኒቨርሲቲው ሲያስተናግድ የቆየው ዓለም አቀፍ የመስክ ኮርስ በስኬት ተጠናቀቀ

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከቤልጂየሙ ʻKU Leuvenʼ፣ ከሲውዘርላንዱ ʻETH Zurichʼ እንዲሁም ከኬንያው ʻEldoretʼ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር ‹‹ምርምርን መሠረት ያደረገ ትምህርት ለዘላቂ የገጠር ልማት›› በሚል መሪ ቃል ዓለም አቀፍ የመስክ ኮርስ ከኅዳር 8/2012 ዓ/ም ጀምሮ ለ15 ቀናት አስተናግዷል፡፡
በመስክ ኮርሱ  30 ተማሪዎችና 6 አማካሪዎች ከአ/ምንጭ ዩኒቨርሲቲ፣ 21 ተማሪዎችና 8 ፕሮፌሰሮች ከቤልጂየሙ ʻKU-Leuvenʼ፣ 15 ተማሪዎችና 3 ፕሮፌሰሮች ከሲውዘርላንዱ ʻETH-Zurichʼ እንዲሁም 4 ፕሮፌሰሮች ከኬንያው ʻEldoretʼ ዩኒቨርሲቲ ተሳትፈዋል፡፡Click here to see the pictures


ለሁለት ሣምንታት በዩኒቨርሲቲው አስተናጋጅነት ሲካሄድ የቆየው የመስክ ትምህርት ዩኒቨርሲቲዎች ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ሥርዓተ-ትምህርቶች እንዲኖራቸው ማድረግን ያለመ መሆኑን የምርምርና ማኅበረሰብ አገ/ት ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ስምዖን ሽብሩ ጠቅሰዋል፡፡ በፕሮግራሙ ተማሪዎችና መምህራኑ በርካታ ልምዶችን ያገኙበት በመሆኑ መሰል ፕሮግራሞች የዩኒቨርሲቲያችን ሥርዓተ ትምህርት አካል እንዲሆኑ ይሠራል ብለዋል፡፡
ም/ፕሬዝደንቱ አክለው የተለያየ ባህል፣ አኗኗር እንዲሁም ማኅበራዊና  ኢኮኖሚያዊ መሠረት ካላቸው ቦታዎች የሚመጡ ተማሪዎች በጋራ የመኖርና የመሥራት ዕድል ስለሚያገኙ መሰል ዓለም አቀፍ የመስክ ኮርሶች የልምድ፣ የዕውቀትና የባህል ልውውጥ እንዲኖር ስለሚያደርጉ ጠቀሜታቸው ጉልህ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡
ከአውሮፓ ሲወጣ የመጀመሪያው እንደሆነ የሚናገረው የቤልጂየሙ ʻKU-Leuvenʼ ዩኒቨርሲቲ የባዮ - ሣይንስ ኢንጂነሪንግ ተማሪ ማትያስ ዴፎርት በአርባ ምንጭና አካባቢው በነበረው ቆይታ ደስተኛ መሆኑን እንዲሁም በመስክ ቆይታው ለትምህርቱ አጋዥ የሆኑ ቁም ነገሮችን ማግኘቱን ተናግሯል፡፡
በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የዕጽዋት ሣይንስ የ2ኛ ዲግሪ ተማሪ ምስጋና ይስሃቅ በበኩሏ በመስክ ቆይታቸው በክፍል ውስጥ በፅንሰ ሃሳብ ደረጃ የተማረችውን በተግባር መፈተሽ እንደቻለች ገልጻ በዚሁ የመስክ ኮርስ ከአውሮፓ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ከመጡ ተማሪዎች ጋር በጋራ መሥራት በመቻሏ ከተማሪዎቹ የአዳዲስ ሶፍትዌሮች አጠቃቀምን ጨምሮ ሌሎች ልምዶችን ማግኘቷን ተናግራለች፡፡
ከመስክ ኮርሱ አስተባባሪዎች መካከል አንዱ የሆኑት በዩኒቨርሲቲው የኅትመት፣ ስነዳና ስርጭት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር  ዶ/ር ገናዬ ፀጋዬ በበኩላቸው የመስክ ኮርሱ እስከ አሁን ባለው ሂደት በተያዘለት ዕቅድ መሠረት መከናወኑን ገልፀው ተማሪዎቹ በመስክ ቆይታቸው በርካታ አዳዲስ ልምዶችን እንዲሁም ወደ ፊት ለሚያከናውኑት የምርምር ሥራ አጋዥ የሆኑ ዕውቀቶችን  እንዳገኙ ከተማሪዎቹ ሪፖርት ማወቅ እንዳቻሉ ተናግረዋል፡፡ ከሪፖርቱ በመነሳት የመስክ ኮርሱ ከታለመለት ዓላማና ግብ አንፃር የተሳካ ነውም ብለዋል፡፡ 
በመስክ ኮርሱ ላይ የተሳተፉ ተማሪዎች ከአማካሪዎቻቸውና ከዩኒቨርሲቲው አመራሮች ጋር በመሆን በዋናው ግቢ በስማቸው በተሰየመ ፓርክ ላይ ኅዳር 18/2012 ዓ/ም ችግኝ ተከላ ያካሄዱ ሲሆን በፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ዩኒቨርሲቲው ይህንን ዓለም አቀፍ ፕሮግራም በማስተናገዱ  በርካታ ልምዶችን ያገኘበት መሆኑን ጠቅሰው በተለይ ፕሮግራሙ ትምህርትን ከምርምር ጋር አቀናጅቶ ማስኬድ የሚለውን መርህ የተከተለ በመሆኑ የመማር ማስተማሩን ሥራ የሚያግዝ መሆኑንን ተናግረዋል፡፡
ከቤልጂየሙ ʻKU Leuvenʼ እና ከሲውዘርላንዱ ʻETH Zurichʼ የመጡ ፕሮፌሰሮችና የፕሮግራሙ አስተባባሪዎች በሰጡት አስተያየት አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሮግራሙን በጥሩ ሁኔታ ማስተናገዱን ገልፀው ተማሪዎቻቸውም ሆነ አማካሪዎቻቸው በርካታ ጥቅሞችን ያገኙበት እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ያሳየው ቁርጠኝነት ፕሮግራሙ በስኬት እንዲካሄድ አድርጓል ያሉት ፕሮፌሰሮቹ ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር መሥራታቸው ትክክለኛ ምርጫ መሆኑን መገንዘባቸውን ገልፀዋል፡፡
ጨንቻ፣ ዶርዜ፣ ጫኖ ዶርጋ፣ ላንቴ፣ ምዕራብ ዓባያ፣ ገረሴና ደንብሌ ተማሪዎቹ ከአማካሪዎቻቸው ጋር መስክ ላይ የቆዩባቸው ቦታዎች ሲሆኑ በፕሮግራሙ ማጠቃለያ ዩኒቨርሲቲው ለተሳታፊዎች የተለያዩ የማስታወሻ ስጦታዎችን አበርክቷል፡፡
ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት