የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን በሲቪል ምህንድስና ሥር እየተሰጡ ባሉ የ2ኛ ዲግሪ ፕሮግራሞች አፈፃፀም ሂደት ላይ ውይይት አካሄደ

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን /ERA/ ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በአገሪቱ ውስጥ ከሚገኙ 7 ዩኒቨርሲቲዎች ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩቶች ከተወጣጡ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በሲቪል ምህንድስና ሥር እየተሰጡ ባሉ የ2ኛ ዲግሪ ፕሮግራሞች አፈፃፀም ሂደት ላይ ኅዳር 19/2012 ዓ/ም በኃይሌ ሪዞርት ውይይት አካሂዷል፡፡Click here to see the pictures

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በመክፈቻ ንግግራቸው እንደገለፁት በአገራችን በ2ኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን ዩኒቨርሲቲው የድኅረ ምረቃ ፕግራሞችን ለማስፋፋትና ለማጠናከር በልዩ ትኩረት ሲሠራ መቆየቱን ጠቁመው ይህንንም ለማሳደግና ለማጠናከር የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ከፍተኛ ድርሻ እንደነበረው ተናግረዋል፡፡ በተለይ በኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ፕሮግራም የ2ኛ ዲግሪ ተከፍቶ ትምህርት እንዲሰጥ መደረጉ ለአገሪቱ ልማት ከፍተኛ የሆነ የባለሙያ ፍላጎት ባለበት ዘርፍ ላይ ዩኒቨርሲቲው አስተዋፅኦ እንዲያደርግ ያገዘው ሲሆን ፕሮግራሙ በዩኒቨርሲቲው በመከፈቱ የአውራ ጎዳና ቤተ-ሙከራ በተሻለ መልኩ እንዲደራጅ ባለሥልጣን መ/ቤቱ የመሣሪያዎች ድጋፍ አድርጓል ብለዋል፡፡ በቀጣይም ባለስልጣን መ/ቤቱ በማስተማር ዘርፍ ብቻ ሳይሆን በምርምርና በሌሎችም ዘርፎች በጋራ ሠርተው ለአገር እድገት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ትብብር ያደርግ ዘንድ ጠይቀዋል፡፡

በዋናነት የመንገድ ሥራን በተመለከተ ከፍተኛ ባለሙያን በማሰልጠን በመንገዶች፣ በህንፃና ግንባታ እንዲሁም በውኃ መሠረተ ልማት ግንባታ ዘርፍ ያለውን ከፍተኛ የሰው ኃይል እጥረት ለመቅረፍ በኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን አማካይነት ከ2005 ዓ/ም ጀምሮ በ7 ዩኒቨርሲቲዎች የ2ኛ ዲግሪ ፕሮግራም መሰጠት መጀመሩን የአ/ም/ዩ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሣይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር አለማየሁ ጩፋሞ ገልጸዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት መ/ር መልካሙ ተሾመ ዩኒቨርሲቲው ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ጋር ባደረገው ትስስር ያለውን የሥራ አፈፃፀም ከተመራቂ ተማሪዎች፣ ከፕሮግራሞች፣ ከመ/ራን ቁጥርና ከቤተ-ሙከራ አንፃር እንዲሁም ከአገር አቀፍና ዓለም ዓቀፍ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ያላቸውን ግንኙነቶች አስመልክቶ ዝርዝር ሪፖርት አቅርበዋል፡፡ በሂደቱም ካጋጠሟቸው ችግሮች መካከል የምርምር በጀት ማነስ፣ የመ/ራንና የግብዓት እጥረት፣ የተማሪዎች በተለያዩ ምክንያቶች ትምህርታቸውን ማቋረጥ፣ የላቦራቶሪ ግብዓቶች በበቂ ሁኔታ አለመሟላት ተጠቃሾች ናቸው ብለዋል፡፡ በተጨማሪም በሌሎች 6 ዩኒቨርሲቲዎች የነበረው የሥራ አፈፃፀም ሂደትና ያጋጠሙ ችግሮችም በዝርዝር ቀርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን የኮርፖሬት አገልግሎት ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ሲሳይ በቀለ እንደገለፁት ፕሮጀክቱ የምህንድስናና የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን አቅም ለማሳደግ የተቀረፀ ፕሮግራም ሲሆን አስተዋፅኦውም በጀት በማስመደብ እንዲሁም ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ያለውን የአቅም ክፍተት በመለየት መገንባት ነው፡፡ በተጨማሪም ከቤተ-ሙከራ ጀምሮ አስፈላጊ ግብዓቶችን ሲያሟላና ዩኒቨርሲቲዎቹ ከሌሎች አገሮች ልምድ አግኝተው ፕሮግራሙን መምራት እንዲችሉ የቅርብ ክትትልና ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ገልፀዋል፡፡ ፕሮግራሙ ሰኔ 2012 ዓ/ም ስለሚጠናቀቅ የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም ሁሉም ተማሪዎች የጀመሩትን ትምህርት ማጠናቀቅ እንደሚገባቸው ተናግረው በታቀደው መሠረት እንዲመረቁ ሁሉም የሚመለከታቸው የዩኒቨርሲቲው ኃላፊዎች ግፊት ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር ያለውን ግንኙነት በሌላ ፕሮጀክት አጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል ያሉት የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የሰው ሀብት ልማትና ማኔጅመንት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል ግርማ 2ኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራም በውሉ መሠረት የሚጠናቀቅ በመሆኑ ከዚህ ቀደም የታዩ ክፍተቶች ላይ አስፈላጊውን የማሻሻያና የእርምት እርምጃ በመውሰድ ባለስልጣኑ የሚጠበቅበትን ለማድረግ ጥረት እንደሚያደርግ አቶ ዳንኤል ተናግረዋል፡፡

በፕሮግራሙ ከአዲስ አበባ፣ ጅማ፣ መቐለ፣ ሀዋሳ፣ ባህር ዳር እና አዲስ አበባ ሣይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም  ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የመጡ የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት