ከ7 ወረዳዎች ለተወጣጡ ሞዴል አርሶ አደሮችና የግብርና ባለሙያዎች በእንስሳት ሥነ-ምግብና የወተት ምርት ማሻሻል ዙሪያ ሥልጠና ተሰጠ

የዩኒቨርሲቲው ‹AMU-IUC› ፕሮግራም የፕሮጀክት-5 ጥናትን መሠረት በማድረግ ከ7 ወረዳዎች ለተወጣጡ ሞዴል አርሶ አደሮችና የግብርና ባለሙያዎች እንዲሁም የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎች በእንስሳት ሥነ-ምግብና የወተት ምርት ማሻሻል ዙሪያ ከኅዳር 22-23/2012 ዓ/ም ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡Click here to see the pictures


የመኖ አጠቃቀምና ዓይነቶች፣ ሥነ-ምግብ፣ የደረቅ ወቅት የመኖ አጠቃቀም፣ የወተት ዝርያ ላሞችና መኖ አመራረጥ፣ የሰብል ተረፈ ምርቶች አያያዝና የብዝሃ-ንጥረ ነገር መኖ አዘገጃጀትና አጠቃቀም ሥልጠናው የተሰጠባቸው ይዘቶች ናቸው፡፡
የAMU-IUC ፕሮጀክት ኃላፊ ዶ/ር ፋሲል እሸቱ በ‹IUC› ፕሮግራም ከሚሠሩት 6 ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚሠራው ፕሮጀክት-5 መሆኑን አስታውሰው የዛሬውም ሥልጠና በፕሮጀክቱ ጥናት አማካይነት በወተት ምርታማነት ላይ የታዩ ችግሮችን መሠረት በማድረግ ተዘጋጅቷል ብለዋል፡፡
የግብርና ሣይንስ ኮሌጅ ዲንና የፕሮጀክት-5 አስተባባሪ ዶ/ር ይስሃቅ ከቸሮ በበኩላቸው ሥልጠናው የወተት ምርትና ምርታማነትን ማሳደግን ዓላማ አድርጎ እንደተዘጋጀ ገልፀው ከሥልጠናው ዋናኛ ይዘቶች መካከል የብዝሃ-ንጥረ ነገር መኖ አዘገጃጀት ዙሪያ የተሰጠው ሥልጠና ተግባራዊ የሚደረግ ከሆነ የውተት ምርትን ከማሳዳግ አኳያ ሚናው ትልቅ ነው ብለዋል፡፡

 

የብዝሃ-ንጥረ ነገር መኖ የሚዘጋጀው ሞሪኒጋ፣ ሞላሰስ፣ ጨው፣ ሲሚንቶ፣ ውኃ፣ ፉርሽካ እና ዩሪያን በመጠቀም መሆኑን የተናገሩት ዶ/ር ይስሃቅ አሠራሩ በብዙ የአፍሪካ አገራት ተሞክሮ ውጤት ያስመዘገበ ነው ብለዋል፡፡ የምርምር ውጤቶችን ወደ መሬት አውርዶ ሕብረተሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ የውዴታ ግዴታ መሆኑን የጠቆሙት ዶ/ር ይስሃቅ ኮሌጃቸው በዩኒቨርሲቲውም ሆነ በሌሎች የምርምር ተቋማት የተሠሩ የምርምር ውጤቶችንና ቴክኖሎጂዎችን ወደ አርሶ አደሩ እንዲወርዱ እየሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በቤልጅየም GHENT ዩኒቨርሲቲ በእንሳሳት ሕክምና ኮሌጅ የሶስተኛ ዲግሪ ተማሪና በፕሮጀክቱ የምርምር ሥራውን እያከናወነ የሚገኘው ከተማ ወርቁ ‹Nutritional Status of Dairy Cow in South Rift Valley› በሚል ርዕስ የምርምር ሥራውን እያከናወነ መሆኑን ገልፆ ለጥናቱ ያግዘው ዘንድ የላሞችን ደም፣ ወተትና መኖ ናሙና በመውሰድ ጥናቱን እያካሄደ መሆኑን ገልጿል፡፡ ጥናቱ በተደረገባቸው አካባቢዎች በአማካይ ከአንድ ላም በቀን 1.5 ሊትር ወተት ብቻ እንደሚገኝና ይህም እጅግ በጣም አነስተኛ መሆኑን የጠቀሰው ተማሪው ለችግሩ ዋነኛ መንስዔ የወተት ላሞቹ የተመጣጠነና የወተት ምርትን ከፍ የሚያደርጉ ምግብ አለማግኘታቸው መሆኑን ተናግሯል፡፡ ለአርሶ አደሮቹ የተሰጠው ሥልጠና የጥናቱን ውጤት መሠረት በማድረግ እንደተዘጋጀና ሠልጣኞች ከሥልጠናው በኋላ የሚያመጡትን ውጤት መከታተልና ውጤታማነቱን ማረጋገጥ ቀጣዩ የፕሮጀክቱ ሥራ ነውም ብሏል፡፡
የሥልጠናው ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት በወተት ላሞች አመጋገብ ዙሪያ ጥሩ ግንዛቤ ማግኘታቸውን ገልፀው በተለይ ሥልጠናው በተግባር የታገዘ መሆኑ ይዘቱ ግልፅ እንዲሆንላቸው ማስቻሉን ተናግረዋል፡፡ የተሰጣቸው ሥልጠና የወተት ምርትን ለማሳደግ የሚረዳ በመሆኑ ሥልጠናውን ተግባራዊ በማድረግ ውጤቱን ለማየት ጓግተናልም ብለዋል፡፡
በሥልጠናው ላይ ተማሪዎቹን ጨምሮ ከአርባ ምንጭ ዙሪያ፣ ጨንቻ፣ ቦረዳ፣ ምዕራብ አባያና ደራሼ ወረዳዎች እና ከአርባ ምንጭ ከተማ የተወጣጡ አርሶ አደሮችና የግብርና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡
ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት