በዓለም 28ኛው በአገራችን 14ኛው ዓለም አቀፍ የነጭ ሪባን ቀን ‹‹በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ የኃይል ጥቃቶችን በመከላከልና በማስቆም አጋርነታችንን እናሳይ!›› በሚል መሪ ቃል በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት አዘጋጅነት ኅዳር 30/2012 ዓ/ም በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል፡፡ምስሉን ለማየት ከዚህ ይጫኑ


የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በመክፈቻ ንግግራቸው እንደገለፁት የነጭ ሪባን ቀንን በየዓመቱ በተቋማችን ስናከብር ከፆታ እኩልነትና ጥቃት፣ ሴቶችን በተለያዩ ዘርፎች ላይ ከማሳተፍ፣ ሴት ተማሪዎችን ውጤታማ ለማድረግ የማጠናከሪያ ትምህርት ከመስጠት እና የሴት መምህራንን ተሳትፎና የምርምር አቅማቸውን ከማሳደግ አንፃር ምን ያህል እየሠራን እንዳለን እራሳችንን የምንፈትሽበትና ክፍተቶቻችንን ለማሻሻል ግንዛቤ የምንጨብጥበት ብሎም ቃል የምንገባበት ነው ብለዋል፡፡ አክለውም ተማሪዎች ከተለያዩ አካባቢዎች የተለያዩ የኑሮ ሁኔታዎችን አልፈው የመጡ በመሆናቸው ውጤታማ እንዲሆኑ ሁሉም የበኩሉን ሚና እንዲጫወት አሳስበው ከፆታ ትንኮሳ የፀዳ ተቋምን ለመፍጠር ሁላችንም ልንሠራ ይገባል ብለዋል፡፡
የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሪት ሠናይት ሳህሌ የነጭ ሪባን መደረግ ዋነኛ ምክንያት  ወንዶች በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ማንኛውንም ጥቃት ለመከላከል አጋርነታቸውን የሚገልጹበት እና ኃላፊነት በመውሰድ ፆታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችን ለማስቆምና መሠረታዊ ችግሮችን ለመፍታት ቃል የሚገቡበት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው በየዓመቱ ቀኑን በተለያዩ ፕሮግራሞች እያከበረና ግንዛቤ እየፈጠረ የሚገኝ በመሆኑ ከቀድሞ የተሻለ ተጨባጭ ለውጥ የሚስተዋል ቢሆንም በተቋሙ በርካታ በጥሩ ሥነ-ምግባር የታነፁና ምሳሌ የሚሆኑ እንዳሉ ሁሉ በውጤትና በጥቅማ ጥቅም በማስፈራራት ጥቃት የሚያደርሱ፣ አላስፈላጊ ቃላትን በመጠቀም የሚያንኳስሱ እንዲሁም ጠንካራ ጎናቸውን ከማበረታታትና ከመደገፍ ይልቅ የሚፈጠሩ ጥቃቅን ስህተቶችን በመፈለግ የሚያሳንሱ መኖራቸውን ዳይሬክተሯ ገልጸዋል፡፡ ይህም በሴት ተማሪዎች ውጤት እንዲሁም በመምህራንና ሠራተኞች ተግባር ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያለውና የተቋሙንም ገፅታ የሚያበላሽ በመሆኑ ጉዳዩን በባለቤትነት በመመልከት ጥቃት ወይም ትንኮሳ ከደረሰባቸው ሴቶች ጎን በመቆም ልንረዳቸው እና ጥቃት አድራሾቹም ህጋዊ እርምጃ ተወስዶባቸው እንዲማሩና ለሌሎችም ማስተማሪያ እንዲሆኑ የበኩላችንን አስተዋፅኦ ልናደርግ ይገባል ብለዋል፡፡
የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ታደለ ሸዋ ባቀረቡት ሰነድ ፆታዊ ትንኮሳ ኅብረተሰቡ ለወንዶችና ለሴቶች ካለው የተለያየ አመለካከት፣ ከተዛባና ሥር ከሰደደ ልማዳዊ አተያይና አሠራር እንዲሁም ከሚሰጠው  ቦታ ጋር በተያያዘ የሚፈፀም የኃይል ጥቃት ሲሆን በከፍተኛ ትምህርት ተቋም ውስጥ የሚደርሱ ጥቃቶች የቃላት ትንኮሳ፣ ወሲባዊ ትንኮሳ፣ ወሲባዊ ጥቃት፣ ስድብ፣ ዛቻ፣ ማጣጣልና ማሸማቀቅ እንዲሁም ነፃነትን ማሳጣት መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ችግሮችን ለመቀነስ በተከታታይ ለኅብረተሰቡ ስለሴቶች ትምህርት ጠቀሜታና ጾታዊ ጥቃት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች መሠራታቸውን፣ በጾታዊ ጥቃት ዙሪያ እና ሴት ተማሪዎች በራስ መተማመናቸውን እንዲያሳድጉና ለራሳቸው የሚሰጡትን ግምት በማጎልበት ጥቃቶችን እንዲከላከሉ የህይወት ክሂሎት ሥልጠናን ጨምሮ የተለያዩ ስልጠናዎችን እንዲያገኙ መደረጉን ገልፀዋል፡፡  በተጨማሪም በትምህርት ተቋማት አካባቢ እየተፈፀመ ያለው ወሲባዊ ትንኮሳ ጤናማ የመማር ማስተማር ሂደት እንዳይኖር እንቅፋት እየሆነ በመምጣቱና በተለይም የሴቶችን የትምህርት ተሳትፎ ብቃትና ውጤታማነት የሚያቀጭጭ በመሆኑ ሊወገዝ ይገባል ብለዋል፡፡
የህግ ትምህርት ቤት መምህር አቶ ደረጀ ማሞ እንደገለፁት ወሲባዊ ትንኮሳ ሴቶች ከሚደርሱባቸው በደሎች አንዱ ሲሆን በአብዛኛው የችግሩ ሰለባ የሚሆኑት ከ12-18 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም የሥራ ላይ ወሲባዊ ትንኮሳ ምንነትና የሚያስከትለው ተፅዕኖ እንዲሁም ወሲባዊ ጥቃት በኢትዮጵያ ህግ ማዕቀፍ የሚሉ ርዕሶች ላይ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት