በዜሮ ፕላን ማዕከል አገልግሎት ዙሪያ ውይይትና የመስክ ምልከታ ተካሄደ

የዩኒቨርሲቲው ሁሉ አቀፍ ሴክተር ዳይሬክቶሬት የዜሮ ፕላን ማዕከል ግንባታን በሚመለከት በተከናወኑ ተግባራት ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ታኅሣሥ 2/2012 ዓ.ም ውይይትና የመስክ ምልከታ አካሂዷል፡፡

በመስክ ምልከታው በዋናው ግቢ የሚገኝ የዜሮ ፕላን ማዕከል ምረቃ ተከናውኗል፡፡ ማዕከሉ በዋናነት የባህርይ ለውጥ ትግበራ፣ ድጋፍና እንክብካቤ፣ ጥናትና ምርምር እንዲሁም መዋቅራዊ አደረጃጀት ትግበራ ላይ ይሠራል፡፡ ምስሉን ለማየት ከዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ እንደገለጹት የዜሮ ፕላን ማዕከል ተማሪዎች የተለያዩ እገዛዎችን የሚያገኙበት በመሆኑ በየካምፓሱ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡

ተማሪዎች በየክበባቱ እየተገናኙ እርስ በእርስ በመማማር ከኤች አይ ቪ/ኤድስና ከሥነ-ተዋልዶ ጤና ችግሮች ተጠብቀው ትምህርታቸውን በስኬት እንዲያጠናቅቁ ማስቻል የማዕከሉ ዋና ዓላማ መሆኑን የሁሉ አቀፍ ሴክተር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ መርክነህ መኩሪያ ተናግረዋል፡፡

የሶፍትዌር ኢንጂነሪንግ 5ኛ ዓመት ተማሪና የሪሃቢልቴሽን ክበብ አባል የሆነችው ተማሪ ቃልአብ አዱኛ ማዕከሉ የሴቶችን ጥቃት ዜሮ ለማድረስ እየሠራ ያለ እና ሴት ተማሪዎች በወር አበባ ጊዜ እንዲሁም በሐኪም ማስረጃ የተረጋገጠ ህጋዊ ውርጃ ሲፈጽሙ እገዛ የሚያገኙበትና የሚያገግሙበት ክፍል መሆኑን ገልጻለች፡፡

በዜሮ ፕላን ማዕከል የኢንፎኪን ክበብ አባልና የክበቡ የመጽሔትና የመጽሐፍ አስመላሸ ኮሚቴ አባል የሆነው ተማሪ አባይነህ ጌታነህ እንደተናገረው በ1999 ዓ.ም የተቋቋመው ኢንፎኪን ክበብ በ14 ዓይነት ዘውጎች የተፃፉ የተለያዩ መጽሐፍት ያሉት ሲሆን ተማሪዎች መጽሐፍትን በመዋስ የሚያነቡበትና በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ሃሳብ በማንሸራሸር እርስ በእርስ የሚማማሩበት ክበብ ነው፡፡

በዕለቱ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንትን ጨምሮ ከፍተኛ አመራሮች፣ የሁሉም ካምፓስ ዲኖች፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴና የኢንስፔክሽን ቡድን አባላት፣ የዩኒቨርሲቲው የሥራ ኃላፊዎች፣ የሁሉም ካምፓስ የፀረ ኤች አይ ቪ ቢሮ አስተባባሪዎች፣ የአስተዳደር ሠራተኞች፣ መምህራንና ተማሪዎች ተገኝተዋል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት