የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል መንግሥት ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ከኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ ኤጀንሲ ጋር በ2010/11 በጀት ዓመት በጋሞ፣ በወላይታና በኮንሶ ዞኖች ያካሄደውን የማዕድን አለኝታ ጥናት ውጤት ታኅሣሥ 2/2012 ዓ.ም ለባለድርሻ አካላት ይፋ አድርጓል፡፡ በፕሮግራሙ ላይ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በጋሞ ዞን ገረሴ ወረዳ ከተሌ ቀበሌ ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚውሉ የከበሩ ድንጋዮችና ማዕድናት መገኘታቸውን አስታውቋል፡፡ ምስሉን ለማየት ከዚህ ይጫኑ

በክልሉ የሚገኘውን ማዕድን በዓይነት፣ በመጠንና በቦታ ለይቶ ለክልሉ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ለማሳወቅ ጥናቱ መከናወኑን የዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ቶሌራ ሴዳ ተናግረዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ጂኦሎጂ ትምህርት ክፍል መምህርና የጥናት ቡድኑ አባል ረ/ፕ ጎሳዬ ብርሃኑ እንደገለጹት ጥናቱ በዋናነት ለሴራሚክ ኢንዱስትሪ የሚውሉ የከበሩ ድንጋዮች ላይ ትኩረት በማድረግ የተለያዩ ባለሙያዎችን ባካተቱ 5 ቡድኖች ለ1 ዓመት ያህል የተከናወነ ሲሆን በጥናቱም ከፍተኛ ጥራት ያላቸው ‹Aquamarine›፣ ‹Tourmaline› እና Garnet የተሰኙ የከበሩ የድንጋይ ናሙናዎች እንዲሁም ‹Feldspar› ማዕድን ውጤታማ ግኝት ተመዝግቧል፡፡ ‹Feldspar› ማዕድን ለሴራሚክ እና ብርጭቆ ኢንዱስትሪዎች ግብዓት የሚሆን ማዕድን ሲሆን በአካባቢው ከ101 ሚሊየን ቶን በላይ ክምችት እንዳለ በጥናቱ ታውቋል፡፡

የአካባቢው ወጣቶች በመደራጀት አካፋ፣ ዶማና የመሳሰሉትን ባህላዊ መሣሪያዎች ተጠቅመው በተለይም ‹Aquamarine› የተባለውን ማዕድን እያወጡ መሆኑን የጠቀሱት ረ/ፕ ጎሳዬ ይህም የማዕድኑን ጥራት በከፍተኛ ሁኔታ እየጎዳው ነው ብለዋል፡፡ ማዕድናቱ ጥራታቸውን እንደጠበቁ እንዲወጡ የሚመለከተው አካል ለወጣቶቹ ሥልጠና ቢሰጥ መልካም መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በጥናቱ የማዕድናቱ መገኛ፣ ጥራትና ክምችት በሚገባ የተዳሰሰ በመሆኑ የሚመለከተው የመንግሥት አካል አዋጭ የማውጫ ዘዴ በመለየት ማዕድናቱ የሚወጡበትን ሁኔታ ቢያመቻች ኢንዱስትሪውን በከፍተኛ ሁኔታ የሚጠቅምና ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ረ/ፕ ጎሳዬ ገልጸዋል፡፡

የምርምር ውጤቱን የማኀበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ እና የዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ቶሌራ ሴዳ ዩኒቨርሲቲውን ወክለው ለኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ ኤጀንሲ ተወካይና ለደቡብ ክልል ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ አስረክበዋል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት