ዩኒቨርሲቲው በገረሴ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ታኅሣሥ 14 እና 22/2012 ዓ/ም በ2 ዙሮች ለ 7 እናቶች የተሳካ የማህፀን ውልቃት ቀዶ ጥገና አድርጓል፡፡
የገረሴ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር ወንድወሰን ወርቁ እንደገለጹት በገረሴ ወረዳና አካባቢው  አብዛኛው እናቶች ለማህፀን ውልቃት ይጋለጣሉ፡፡

አካባቢው ለትራንስፖርት አመቺ ባለመሆኑ በቤት ውስጥ በባህላዊ መንገድ መውለድ ከፍተኛ ግፊት ማህፀን ላይ ማሳረፉ እንዲሁም ከባድ ሥራዎችን መሥራት ለህመሙ ከሚያጋልጡ ምክንያቶች መካከል ዋነኞቹ ናቸው፡፡
በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲና በአርባ ምንጭ ሆስፒታል የማህፀንና ፅንስ ስፔሻሊስት ዶ/ር ነጋ ጩፋሞ ሕክምናውን ሲሰጡ እንደተናገሩት የማህፀን ውልቃት እየሰፋ ከመጣባቸው አካባቢዎች አንዱ ገረሴ ሲሆን ገረሴ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ዩኒቨርሲቲውን ትብብር በመጠየቁ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ በ2 ዙሮች በተሳካ ሁኔታ ለእናቶች ነፃ የቀዶ ጥገና አገልግሎት መስጠት መቻሉን ተናግረዋል፡፡ 
ሆስፒታሉ ሌሎች ህክምናዎችን በስፋት እየሰጠ ቢገኝም በተለይ በዚህ ህክምና ዘርፍ በሆስፒታሉ የሰለጠነ ባለሙያ ባለመኖሩና በአካባቢው አብዛኛው እናቶች በግንዛቤ እጥረት በህክምና ተቋማት ካለመውለዳቸው ጋር ተያይዞ የሚከሰትባቸውን የማህፀንና ፅንስ እንዲሁም ተጓዳኝ ችግሮች ለመቀነስ ወደ ማኅበረሰቡ መውረድ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን ዶ/ር ነጋ አስረድተዋል፡፡ በቀጣይ በሌሎች ወረዳዎች ለሚገኙ እናቶችም  ህክምናው እንደሚሰጥ ጠቅሰዋል፡፡ ምስሉን ለማየት ከዚህ ይጫኑ
የገረሴ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ አቶ ስምዖን ሰዳሞ በበኩላቸው የእናቶችና ሕጻናት ጤናን ከማሻሻል አኳያ ዩኒቨርሲቲው በየጊዜው ከሆስፒታሉ ጋር የሚፈጥረው ግንኙነት የሚያበረታታ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ከእናቶች ጤና በተጨማሪ ሌሎች ሕክምናዎችን ለመስጠት ፈቃደኛ ቢሆንም በሆስፒታሉ የተለያዩ መሣሪያዎች እጥረትያለ በመሆኑ የህክምና ድጋፉን በበለጠ ለመስጠት አለመቻሉን አቶ ስምኦን አስረድተዋል፡፡  
ዩኒቨርሲቲው የሆስፒታሉን የጤና ባለሙያዎች በትምህርት ከመደገፍ አኳያ በ2011 ዓ.ም ለ2 የጤና ባለሙያዎች የትምህርት ዕድል መስጠቱን አቶ ስምዖን ጠቅሰው በቀጣይም የሆስፒታሉን የጤና ባለሙያዎች አቅም ለመገንባት ሌሎች የትምህርት ዕድሎችን እንዲፈጥርና የቁሳቁስ እገዛዎችን እንዲያደርግ ዩኒቨርሲቲውን ጠይቀዋል፡፡
ህክምናውን ያገኙ እናቶች ለዓመታት በበሽታው ሲሰቃዩና ከሰው ሲሸሹ መቆየታቸውን ገልጸው ህክምናውን ከአካባቢያቸው ሳይርቁ በማግኘታቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡
ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት