በቁንጭር /የቆዳ ላይ ሌሽማኒያሲስ/ በሽታ ላይ ያተኮሩ የምርምር ሥራዎች ቀርበው ውይይት ተካሄደ

የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማኅ/አገ/ም/ፕ ጽ/ቤት በደጋ ኦቾሎ አካባቢ ላይ ተከስቶ በቆየው ቁንጭር /ሌሽማኒያሲስ/ ወይም በአካባቢው ቋንቋ ‹‹ቦልቦ›› በሽታ ላይ የተካሄዱ የምርምር ሥራዎችን መሠረት በማድረግ ጥር 1/2012 ዓ/ም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይት አካሂዷል፡፡ ምስሉን ለማየት ከዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማኅ/አገ/ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ስምዖን ሽብሩ በአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ በአንዳንድ አካባቢዎች በተለይም በደጋ ኦቾሎ አካባቢ በቁንጭር በሽታ ዙሪያ የተጠኑ ጥናቶች የደረሱበትን ደረጃ ኅብረተሰቡ እንዲያውቅና በቀጣይ ሥራዎች ዙሪያ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመወያየት አቅጣጫ ለማስቀመጥ ውይይቱ ተዘጋጅቷል ብለዋል፡፡

ተባባሪ ፕሮፌሰርና የ 3ኛ ዲግሪ ተማሪ አቶ በኃይሉ መርድኪዮስ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፍ እንደተገለጸው ሌሽማኒያሲስ በባህሪው ጥገኛና በእንስሳ ህዋስ /ሴል/ ውስጥ ገብቶ የሚኖር ሲሆን በአሸዋ ዝንብ (ሳንድ ፍላይ) በተባለ ትንኝ ንክሻ አማካይነት ይተላለፋል፡፡ በሽታው በሰውነት ውስጥ እና በቆዳ ላይ የሚከሰት ሲሆን የውስጥ ብልቶች ሌሽማኒያሲስ በቆላ አካባቢ የሚታይና በአግባቡና በቶሎ ካልታከሙት ጉበትን በመጉዳት እስክ ሞት የሚያደርስ ነው፡፡ ሁለተኛው ዓይነት የቆዳ ላይ፣ የአፍና የአፍንጫ ኅብረ-ህዋስ ሽፋን ሌሽማኒያሲስ /ቁንጭር/ በወይና ደጋማና ደጋማ አካባቢዎች የሚታይ ሲሆን በተለይም ስስ የሆነው የሰውነት ክፍል ላይ እየሰፋ የሚሄድ ቁስል በመፍጠር ዘላቂ የአካልና የሥነ-ልቡና ጉዳት የሚያስከትል ነው፡፡

ቁንጭር በአ/ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ደጋ ኦቾሎ አካባቢ በስፋት የሚታይ ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ መኖሩ በጥናት የታወቀው 1963 ዓ.ም ነው፡፡ በሽታውን አምጪ ተህዋሱ ወደ ሰውነት ከገባ የበሽታው ሙሉ ምልክት እስኪታይ ከወራት እስከ ዓመታት ሊቆይ የሚችል ሲሆን በአገራችን የሚገኘው ቁንጭር በባህሪው ቀስ ብሎ የሚያድግና ቆይቶ የሚቆስል በሂደትም ወደሙሉ የሰውነት አካል ስርጭት ሊለወጥ የሚችል መሆኑን ጥናቶች እንደሚያመላክቱ አቶ በኃይሉ ገልፀዋል፡፡ በበሽታው የሚወጣው ቁስልም በአማካይ ከ1-3 ዓመታት ጊዜ ውስጥ የሚድን መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የአሸዋ ዝንብን የሚከላከሉ አጎበሮችን መጠቀም የትንኞቹን ንክሻ እና የበሽታውን መተላለፍ እንደሚቀንስ በጥናቱ ተጠቁሟል፡፡ ጥናቱ የቁንጭር በሽታን በላቦራቶሪ በፍጥነት ለመለየትና ለማረጋገጥ እንዲቻልና በዘርፉ ለሚደረገው ምርምር እንዲሁም ህክምናውን ለማቀላጠፍ የጎላ ድርሻ እንደሚኖረውም ተገልጿል፡፡

ሌላኛው ጥናታዊ ፅሁፍ አቅራቢ የተፈጥሮ ሣይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ፈቃዱ ማሴቦ ‹‹የቦልቦ በሽታ የመተላለፊያ ሁኔታ በኦቾሎ›› በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጽሑፍ የደጋ ኦቾሎ አካባቢ ድንጋያማ፣ ሞቃታማ እና ለሽኮኮና ለአሸዋ ዝንብ አመቺ የሆነ የመራቢያ ቦታ ያለበት ስፍራ በመሆኑ ለበሽታው መስፋፋት ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በተጨማሪም የአሸዋ ዝንብ ስንጥቅ ያለባቸው ቤቶች፣ የከብቶች እበት መጣያ፣ ድንጋያማና የሽኮኮ ሰገራ ያለባቸው ቦታዎች ላይ የምትራባ በመሆኑ ኅብረተሰቡ እነዚህን ሁኔታዎች በማስተካከል በሽታው የሚቀንስበትን መንገድ ማማቻቸት ይኖርበታል ብለዋል፡፡

የቀረበውን ጥናታዊ ፅሁፍ አስመልክቶ በርካታ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ ከአካባቢው የመጡ ታዳሚዎች በሰጡት አስተያየት ቦልቦ የአካባቢው ማኅበረሰብ አሳሳቢ ችግር ሲሆን መልክን አበላሽቶ ለጋብቻ የደረሱ ልጆችን ሳያገቡ እንዲቆዩ የሚያደርግና የቆዳ ላይ ጠባሳና የአካል ጉዳት በማድረስ ለከፍተኛ የሥነ-ልቡና ጫና የሚዳርግ በመሆኑ ፊት ላይ ከመውጣቱ በፊት ውስጥ እንዳለ የሚያጠፋው መድኃኒት የሚገኝበት መንገድ ቢመቻች ብለዋል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት