የዩኒቨርሲቲው የእንግሊዝኛ ቋንቋና ሥነ-ጽሑፍ ትምህርት ክፍል ከዩኒቨርሲቲው የማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ጋር በመተባበር በንባብ ክሂሎት ላይ ያተኮረ ፕሮጀክት ቀርፀው በምዕራብ አባያና በልማት 1ኛ ደረጃ ት/ቤቶች ለሚገኙ ዝቅተኛ የንባብ ክሂሎት ላላቸው ከ2ኛ - 4ኛ ክፍል ተማሪዎች የእንግሊዝኛ ቋንቋ የንባብ ክሂሎት ማሻሻያ ትምህርት ለመስጠት የቅድመ መለያ ፈተና እየተሰጠ ይገኛል፡፡ ፕሮግራሙ ከጥቅምት 1/2012 ዓ/ም ጀምሮ ተግባራዊ እየተደረገ ሲሆን እስከ ሰኔ 30/2012 ዓ/ም እንደሚቆይም ተጠቁሟል፡፡ምስሉን ለማየት ከዚህ ይጫኑ

የፕሮጀክቱ አስተባባሪና የእንግሊዝኛ ቋንቋ ትምህርት ክፍል መ/ር መለሰ መንገሻ እንደገለፁት ፕሮጀክቱ የምርምር ውጤትን መሠረት ያደረገና የ1ኛ ደረጃ ተማሪዎች የንባብ ችሎታ መሻሻል ላይ ያተኮረ እንዲሁም በውስጡ 4 አባላትን ያቀፈ ሲሆን በእንግሊዝኛ ቋንቋ በጣም ዝቅተኛ የማንበብ ችሎታ ያላቸውን ተማሪዎች ማብቃት መሠረታዊ ዓላማው ነው፡፡ በቀጣይም ውጤቱን መሠረት በማድረግ በጣም ዝቅተኛ የንባብ ክሂሎት ያላቸውን 150 ተማሪዎች በመምረጥ፣ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመወያየትና ለእንግሊዝኛ ቋንቋ መምህራን ስልጠና በመስጠት የተማሪዎችን የእንግሊዝኛ ቋንቋ ንባብ ክሂሎት በማሳደግ የማብቃት ሥራቸውን እንደሚቀጥሉም ገልፀዋል፡፡

የአማርኛ ቋንቋና ሥነ-ጽሑፍ ትምህርት ክፍል መምህር ዶ/ር ኃይላይ ተስፋዬ በበኩላቸው ተማሪዎቹ የመለያ ፈተናውን በሚፈተኑበት ወቅት የሚስተዋሉ በርካታ ችግሮች መኖራቸውን ተናግረው አብዛኛዎቹ ተማሪዎች የጋሞኛ፣ ጎፍኛ፣ ወላይትኛና ኦሮምኛ ቋንቋ አፈ-ፈት እንደ መሆናቸው መጠን የላቲን ሥርዓተ- ጽሕፈት ተጠቃሚ በመሆናቸው የአፍ መፍቻ ቋንቋቸውና እንግሊዝኛ ቋንቋው ይምታታባቸዋል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም በአብዛኛዎቹ ተማሪዎች ፈፅሞ ፊደሉን ያለማወቅ፣ ትክክለኛ ንበቱን /Pronunciation/ በትክክል መጥራት ያለመቻል ችግር እንዲሁም ማንበብ በሚችሉ ተማሪዎች ዘንድም በፊደልም ሆነ በቃል ደረጃ የአፍ መፍቻ ቋንቋ ተፅዕኖዎች እንዳሉ ዶ/ር ኃይላይ ጠቁመዋል፡፡ በተለይም በምዕራብ አባያ 1ኛ ደረጃ ት/ቤት አብዛኛዎቹ ተማሪዎች በቃል ደረጃ አለማንበባቸው በመማሪያ መጽሐፉና በትምህርት ሥርዓቱ ላይ ያለውን ደረጃ እንደማያሟሉ ያሳየናል ብለዋል፡፡ በቀጣይ ችግሩን ለይተው ወደ መፍትሄ የሚያመሩ መሆኑንና ውጤቱን እውን ለማድረግ ከወላጆች ጀምሮ እስከ ትምህርት መምሪያ ድረስ ያሉ አካላት በሙሉ ኃላፊነትን በመውሰድና የበኩላቸውን ድርሻ በመወጣት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ሊያበረክቱ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

የጋሞ ዞን ትምህርት መምሪያ የትምህርት ቤት መሻሻል ፕሮግራም ዳይሬክቶሬት ቡድን መሪ አቶ ጌታቸው ጥላሁን እንደተናገሩት ችግሩ ሰፊ እንደመሆኑ መጠን ግኝቱ በቀጣይ እንዴት መሥራት እንዳለብን አቅጣጫ ሊያሳየን የሚችል ወሳኝ ጥናት ነው ብለዋል፡፡ አስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች ሁሉ ከመምህራኑ ጎን እንደሚሆኑም ገልፀዋል፡፡

በቀጣይ ለት/ቤቱ የእንግሊዝኛ ቋንቋ መምህራን የንባብ ክሂሎት ማሻሻያ ስልጠና እንደሚሰጥና ያገኙትንም እውቀት ተጠቅመው ከፕሮጀክቱ አባላት ጋር በመሆን በተማሪዎቹ ላይ ለ1 ዓመት ተግባራዊ እንደሚያደርጉ የማኅበራዊ ሣይንስና ሥነ-ሰብ ኮሌጅ የማኅበረሰብ አገልግሎት አስተባባሪ መ/ር መሐመድ ሹሬ ተናግረዋል፡፡ የተሻለ ውጤት ከታየ እንደግብዓት በመውሰድ በቀጣይ ዩኒቨርሲቲው ተንቀሳቅሶ በሚሠራባቸው በሁሉም ቦታዎች ላይ አስፍተው እንደሚሠሩና በአተገባበሩም ላይ ከፍተኛ ክትትል እንደሚደረግ ጠቁመዋል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት