የተማሪዎች ኅብረት የፓርላማ አባላትና አመራሮች ምርጫ ተጠናቀቀ

ከታኅሣሥ 14/2012 ዓ/ም ጀምሮ ሲካሄድ የቆየው የተማሪዎች ኅብረት የፓርላማ አባላትና አመራሮች ምርጫ ጥር 03/2012 ዓ/ም የኅብረቱ የሥራ አስፈጻሚ እንዲሁም የኦዲትና ቁጥጥር ኮሚቴ አባላትን በመምረጥ ተጠናቋል፡፡

በዚህ መሠረት ተማሪ አንዳርጋቸው ደስታ የኅብረቱ ፕሬዝደንት፣ ተማሪ የትምወርቅ ክብሩ ም/ፕሬዝደንት እንዲሁም ተማሪ ቃልኪዳን አባይነህ ዋና ፀሐፊ በመሆን ተመርጠዋል፡፡ በተጨማሪም ተማሪ ገነት ካሳዬ፣ ተማሪ ሀለፎም ደረጀ እና ተማሪ ሚልኪያስ ሙርቴ የኦዲትና ቁጥጥር ኮሚቴ አባላት ሆነው ተመርጠዋል፡፡ ምስሉን ለማየት ከዚህ ይጫኑ

የኅብረቱ ፕሬዝደንት ተማሪ አንዳርጋቸው ደስታ ምርጫው በሰላማዊ መንገድ እንደተጠናቀቀ ገልጾ የውይይት ባህል በተማሪዎች ዘንድ በማዳበር አልፎ አልፎ የሚነሱ ጥያቄዎችን ከዩኒቨርሲቲው አመራሮች ጋር በመወያየት የመፍትሄ አቅጣጫ ማስቀመጥ ተገቢ እንደሆነ ተናግሯል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በአገሪቱ ካሉ 8 የምርምር ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ መደረጉ የትምህርት አሰጣጡ በተሻለ ሁኔታ በተግባር እንዲደገፍና ተማሪዎች የማኅበረሰቡን ችግር የሚፈቱ ጥናትና ምርምሮችን ለማከናወን የሚያስችል አቅም ለማጎልበትና የፈጠራ ችሎታ ለማዳበር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅትና በትኩረት ሊሠሩ ይገባል ብሏል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ አስመራጭ ኮሚቴውና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ምርጫው ነፃ፣ ፍትሐዊና ዲሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ለተጫወቱት ሚና ምስጋና በማቅረብ ሁሉንም ተማሪዎች የሚወክሉና ብቁ የኅብረቱ አመራሮችን በማስመረጥ የተደራጀና ጠንካራ የተማሪዎች ኅብረት በዩኒቨርሲቲው እንዲቋቋም ማስቻል ሰላማዊ የመማር-ማስተማር ሂደትን ለማረጋገጥና ለማስቀጠል እንደሚረዳ ተናግረዋል፡፡ ተማሪዎች የአመራርነት ክሂሎት በማዳበር በትምህርታቸው ውጤታማ እንዲሆኑና የተጓዳኝ እውቀትና ክሂሎት ባለቤት እንዲሆኑ የሚደግፍ ነውም ብለዋል፡፡ ፓርላማው የ20ሺ ተማሪዎች ተወካይ እንደመሆኑ መጠን ተቀራርቦ በውይይትና ቅንጅት መሥራት እንዳለበት ገልጸው የሥራ አስፈጻሚዎችም በተመሳሳይ መልኩ የወከሏቸውን ተማሪዎች በታማኝነትና በቅንነት እንዲያገለግሉ አሳስበዋል፡፡

የተማሪዎች አገልግሎት ማዕከል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አየልኝ ጎታ በበኩላቸው የ2012 የትምህርት ዘመን የተማሪዎች ኅብረት የፓርላማ አባላትና አመራሮች ምርጫ ለማድረግ መመሪያውንና የማስፈፀሚያ የድርጊት መርሃ-ግብሩን ሁሉም ተማሪ አስቀድሞ ከዩኒቨርሲቲው ኢንትራኔት እንዲያገኝ ተደርጓል ብለዋል፡፡ በመቀጠልም ከሁሉም ካምፓስ የሴክሽን ተጠሪ ወንድና ሴት ሁለት ተማሪዎች በውጤታቸው መሠረት እንዲመረጡ እንደተደረገ ገልፀዋል፡፡ መመሪያውን በመመርኮዝ ለብሔርና ለሴቶች ተሳትፎ ትኩረት ተሰጥቶ 16 ተማሪዎች ለፈተና የቀረቡ ሲሆን 8ት ተማሪዎች በፈተና ውጤት ተለይተው ለሥራ አስፈጻሚነት ተወዳድረዋል፡፡ ተማሪዎቹ ለሁለት ዓመት የሚቆይ የየራሳቸውን የስትራቴጅክ ዕቅድ ለ10 ደቂቃ እንዲያቀርቡና በዕቅዳቸው ዙሪያ ከፓርላማው ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲሰጡ ተደርጎ ባገኙት አጠቃላይ ውጤት መሠረት የምርጫው ውጤት ይፋ መደረጉን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

የስትራቴጂክ ዕቅድ ትግበራና ክትትል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አስፋው ደምሴ እንደገለጹት ለዋና የሥራ አስፈፃሚነት የተወዳደሩ ዕጩ ተመራጮች የትምህርት ውጤት CGPA 2.75 እና ከዚያ በላይ ያስመዘገቡ፣ መልካም ሥነ-ምግባር ያላቸው፣ ማንኛውም የዲስፕሊን ጥሰት ያልተመዘገበባቸው፣ የተማሪውን ጥቅም ከዩኒቨርሲቲውና ከአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ

ጋር ማገናዘብ የሚችሉ፣ የተማሪዎች መብት እንዲከበርና ግዴታቸውን አንዲወጡ የሚያደርጉ፣ የተግባቦትና የራስ መተማመን ችሎታ ያላቸው፣ በፖለቲካ አመለካከት አድልኦ የማያደርጉ እንዲሁም በኃይማኖትና በብሔር ምክንያት ምንም ዓይነት ልዩነት የማያንፀባርቁ ስለመሆናቸው በባለድርሻ አካላት ተጠንቶ በታማኝነት እንደሚያገለግሉ የታመኑ ናቸው ብለዋል፡፡

በተጨማሪም በተለያዩ የተማሪ አደረጃጀቶች ተሳትፎ የምስክር ወረቀት ያላቸው እንዲሁም በጽሁፍ ፈተና፣ በቃለ መጠይቅ፣ በስትራቴጂክ ዕቅድ ሰነድ ዝግጅት ግምገማ ከ40 በመቶ እና በፓርላማው ድምፅ ከ60 በመቶ በአጠቃላይ ባገኙት ድምር ውጤት መሠረት ዋና የሥራ አስፈፃሚዎች እንደተመረጡ አቶ አስፋው ተናግረዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ቢዝነስና ልማት ም/ፕሬዝደንትና የተማሪዎች ኅብረት የፓርላማ አባላትና አመራሮች ምርጫ ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ ታሪኳ ወ/መድኅን በሰጡት አስተያየት ምርጫው የመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተማሪዎች ኅብረት አደረጃጀትና ምርጫ አፈጻጸም መመሪያ ቁጥር-003/2012 ዓ/ም መሠረት ያደረገ በመሆኑ በሁሉም ተማሪዎች ዘንድ ተቀባይነት አግኝቶ ያለ አንዳች ቅሬታ እንደተጠናቀቀ ገልጸዋል፡፡ የኅብረቱ አመራር ምርጫ በውድድር መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በዋና ሥራ አስፈጻሚና የዘርፍ ሥራ አስፈፃሚ ኅብረ-ብሄራዊ ለማድረግና የሴቶችን ተሳትፎ ለማረጋገጥ አንቀፅ 24ን መሠረት ያደረገ ነው ብለዋል፡፡

በሣይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የተዘጋጀው መመሪያ በውስጡ 8 ክፍሎችና 48 አንቀፆችን የያዘ ሲሆን በዚሁ መሠረት የኅብረቱ መሠረታዊ አደረጃጀት መዋቅር ጠቅላላ ጉባኤ (ፓርላማ) በሥሩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ፣ አፈ-ጉባኤ እና ኦዲትና ቁጥጥር አባላት ያካትታል፡፡ ዋና ሥራ አስፈጻሚውም የአካዳሚክ፣ የህዝብ ግንኙነት፣ የዲስፕሊን፣ የጤና፣ የልዩ ፍላጎት፣ የምግብ፣ የፋይናንስ፣ የሴቶች ጉዳይ፣ የጠቅላላ አገልግሎት፣ የክበባትና ማኅበራት፣ የስፖርትና መዝናኛ እንዲሁም የበጎ አድራጎት ዘርፎችን ይይዛል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት