የዩኒቨርሲቲው ሕግ ት/ቤት ከእንግሊዙ ኦክስፎርድ ብሩክስ (Oxford Brookes) ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ እየሠራ ነው

የዩኒቨርሲቲው ሕግ ት/ቤት ከእንግሊዙ ኦክስፎርድ ብሩክስ /Oxford Brookes/ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመማር ማስተማር፣ በምርምርና በመምህራን ልማት ላይ በጋራ እየሠራ መሆኑን ገልጿል፡፡ በዚህም መሠረት ከኦክስፎረድ ብሩክስ ዩኒቨርሲቲ የመጡ ተማሪዎችና ፕሮፌሰሮች ከዩኒቨርሲቲው ሕግ ት/ቤት ተማሪዎች ጋር የጋራ የመስክ ትምህርት እየተከታተሉ ይገኛሉ፡፡ ምስሉን ለማየት ከዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር የቻለ ከበደ ዩኒቨርሲቲው ከምሥረታው ጀምሮ በመማር ማስተማር፣ በምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት እያከናወናቸው ባሉ ተግባራት ዙሪያና በሌሎች አካባቢያዊና አገራዊ ጉዳዮች ላይ ለተማሪዎቹና ለፕሮፌሰሮቹ ጥር 5/2012 ዓ/ም ገለጻ አቅርበዋል፡፡

ዶ/ር የቻለ በገለጻቸው ዩኒቨርሲቲው ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር የዩኒቨርሲቲውን ዋነኛ ተልዕኮዎች መሠረት በማድረግ በጋራ እየሠራ መሆኑን ጠቅሰው በቀጣይም የጋራ ተጠቃሚነትን መሠረት ባደረገ መልኩ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ዩኒቨርሲቲዎችና የምርምር ተቋማት ጋር መሥራቱን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

የሕግ ት/ቤት ዲን አቶ ደርሶልኝ የኔአባት በበኩላቸው በተማሪዎችና መምህራን ልውውጥ እንዲሁም በምርምር ሥራ ላይ በጋራ ለመሥራት እ.አ.አ በ2018 ዓ/ም ከዩኒቨርሲቲው ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈርሞ እንደ ነበር አስታውሰው በዚሁ መሠረት ከዩኒቨርሲቲው የመጡ ፕሮፌሰሮች ተማሪዎቻችንን በማስተማርና የጥናት አማካሪ በመሆን እየሠሩ ነው ብለዋል፡፡ በተጨማሪም የት/ቤቱ መምህራን የ3ኛ ዲግሪ የትምህርት ዕድል በዩኒቨርሲቲው እንዲሰጣቸው እየተሠራ እንደሆነም ገልፀዋል፡፡ የጋራ የመስክ ትምህርቱ የስምምነቱ አካል ሲሆን በቀጣይም የት/ቤቱ ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲው ሄደው በጋራ የመስክ ትምህርት ላይ እንዲሳተፉ ይደረጋል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም በት/ቤቱ አዘጋጅነት ከኦክስፎርድ ብሩክስ ዩኒቨርሲቲ በመጡ ፕሮፌሰሮች ‹‹Does Torture Prevention Work?›› በሚል ርዕስ በጥናት ላይ የተመሠረተ ፐብሊክ ሌክቸር ጥር 8/2012 ዓ/ም የቀረበ ሲሆን በፕሮግራሙ ላይ የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንትን ጨምሮ የት/ቤቱ ዲን፣ መምህራንና ተማሪዎች እንዲሁም ከአርባ ምንጭ ማረሚያ ተቋም የተወጣጡ የፖሊስ አባላትና ሌሎች ከከተማና ከዞን መዋቅር የተወጣጡ የፍትህ አካላት ተገኝተዋል፡፡

የአካዳሚክ ጉ/ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር የቻለ ከበደ በመክፈቻ ንግግራቸው መሰል ፕሮግራሞች የተሻለ የመማር ማስተማር ሥራ እንዲኖር የሚያግዙ መሆናቸውን ገልፀው በተለይ ከኦክስፎርድ ብሩክስ ዩኒቨርሲቲ ጋር የተጀመረውን ትብብር አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ብለዋል፡፡

ገለጻውን ካቀረቡት ፕሮፌሰሮች አንዱ Proff. Richard Garver በዓለም ላይ በሚገኙ 16 አገራት ከ1985-2014 ዓ/ም ባሉ 30 ዓመታት ውስጥ በእስረኞች እና በተጠርጣሪዎች ላይ መረጃ ለማግኘት ሲባል በፍትሕ አካላት የሚፈፀሙ አካላዊ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶችን መከላከል ይቻላል ወይስ አይቻልም በሚሉ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገው ጥናቱን እንደሠሩ ተናግረዋል፡፡ እንደ ፕሮፌሰሩ ገለጻ በእነዚህ 30 ዓመታት በአገራቱ በእስረኞችና በተጠርጣሪዎች ላይ የሚፈፀሙ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶች እየቀነሱ መምጣታቸውን በጥናቱ አረጋግጠናል ብለዋል፡፡

የፍትህ አካላት በተለይ ፖሊሶች የተፈፀመ ወንጀልን ለማወጣጣት ሲባል ኃይልን የሚጠቀሙት በሣይንሳዊ ዘዴዎች ወንጀልን የመመርመር ክሂሎት ስለሌላቸው መሆኑን የጠቆሙት ፕሮፌሰሩ የወንጀል መርማሪዎችን አቅም ለማጎልበት በስፋትና በጥልቀት ስልጠና መስጠት እንዲሁም ለምርመራ ሲባል የተለያዩ ማሰቃያ ዘዴዎችን የሚጠቀሙ አካላትን ተጠያቂ በማድረግ ድርጊቱን ማስቆም ይቻላል ብለዋል፡፡

ከፕሮግራሙ ተሳታፊዎች መካከል በዩኒቨርሲቲው የ2ኛ ዲግሪ የሕግ ተማሪ ቦንካሾ ሀንጌ በሰጠው አስተያየት ከፕሮፌሰሮቹ ገለጻ ጠቃሚ እውቀት እንዳገኙ ገልጸው እንደ አገር በሕግ ቁጥጥር ሥር የሚገኙ ግለሰቦች ላይ የሚፈፀሙ አካላዊና ሥነ-ልቦናዊ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶችን ለማስቀረት በዘርፉ የሚሠሩ ባለሙያዎችን ሣይንሳዊ የምርመራ ዘዴዎችን እንዲጠቀሙ ማሰልጠን ይገባል ብሏል፡፡

የመስክ ትምህርቱ ተሳታፊ የሆኑት የኦክስፎርድ ብሩክስ ዩኒቨርሲቲ መምህራንና ተማሪዎች በበኩላቸው በዩኒቨርሲቲው ቆይታቸው በርካታ አዳዲስ ልምዶችን እንዳገኙና በዩኒቨርሲቲው አጠቃላይ አደረጃጀትና የመማር ማስተማር ሂደት እንደተደነቁ ገልፀዋል፡፡ በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲው በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂና ተወዳዳሪ ለመሆን በትኩረት እንዲሠራም አሳስበዋል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት