የዩኒቨርሲቲው ካውንስል ከሣይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በወረዱ አዳዲስ መመሪያዎችና የሥራ አቅጣጫዎች እንዲሁም በዘርፉ የቀጣይ 10 ዓመታት ዕቅድ ዙሪያ ጥር 5/20112 ዓ/ም ውይይት አካሂዷል፡፡

ሠላማዊ የመማር ማስተማር ሂደትን ማስፈንና ማዝለቅ፣ ዩኒቨርሲቲዎችን በመስክና በተልዕኮ መለየት፣ የከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ የትምህርትና ሥልጠና ለውጥ ሥራዎች ትግበራና ቀጣይ ሥራዎች፣ ICTን ለመማር ማስተማር፣ ለምርምርና ለተቋም አስተዳደር ማዋልና ቀጣይ ትኩረት አቅጣጫዎች እንዲሁም የሣይንስ፣ የምርምርና የማኅበረሰብ አገልግሎት ሪፎርም አተገባበር ውይይቱ ከተደረገባቸው ዓበይት ጉዳዮች መካካል ናቸው፡፡ ምስሉን ለማየት ከዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በዩኒቨርሲቲዎች እንደ አገር ሠላማዊ መማር ማስተማር ሂደትን ማስፈን ፈታኝ ሆኖ እንደቆየ አስታውሰው ነገር ግን በዩኒቨርሲቲያችን የሚስተዋለውን ሠላማዊ ሂደት ለማዝለቅ እንደ ከዚህ ቀደሙ ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር በመሆን በትኩረት ልንሠራ ይገባል ብለዋል፡፡

የአካዳሚክ ጉ/ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር የቻለ ከበደ በበኩላቸው በ2012 የትምህርት ዘመን ለመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎች እየተሰጡ ያሉ የጋራ ኮርሶች ጉዳይ እንደ አገር ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው እስካሁን እንደ ዩኒቨርሲቲ ሥራው የተመራበት አግባብ የሚበረታታ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በቀጣይ ተማሪዎቹን በየትምህርት መስኩ የመመደብና የምዘና ሂደት በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በተቀመጠው መመሪያ መሠረት ለመፈፀም በጥንቃቄ ልንሠራ ይገባል ብለዋል፡፡

በውይይቱ ዩኒቨርሲቲው የምርምር ዩኒቨርሲቲ ሆኖ መለየቱ ያለው አንድምታ፣ ለምርምርና ቤተ-ሙከራ የሚሆኑ ቁሳቁሶች ግዥ መዘግየት፣ የጋራ ኮርሶች አሰጣጥና ምዘና ሥርዓት ዙሪያ እየገጠሙ ያሉ ችግሮች፣ በአዲሱ የሠራተኞች የነጥብ ምዘናና ደረጃ አወሳሰን ዘዴ በአግባቡ ያልተጠኑ የሥራ መደቦች ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች በተሳታፊዎች ቀርበዋል፡፡

በዕለቱ ውይይቱን ሲመሩ የነበሩት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛና የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር የቻለ ከበደ በሰጡት ምላሽ ዩኒቨርሲቲው የምርምር ዩኒቨርሲቲ በመደረጉ ማስተማር የሚያቆም አለመሆኑን ገልፀው በአንፃሩ ለምርምር ዘርፉ ትኩረት እንደሚሰጥና የመማር ማስተማሩ ሥራ ምርምር ተኮር ሆኖ የድኅረ ምረቃ ፕሮግራሞችን ለማስፋፋት ትኩረት ይሰጣል ብለዋል፡፡ የጋራ ኮርሶች አሰጣጥና ምዘና ሂደት በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በተቀመጠው አቅጣጫና መመሪያ መሠረት መፈፀም ያለበት መሆኑን የጠቀሱት ኃላፊዎቹ ከአዲሱ የሠራተኞች የነጥብ ምዘናና ደረጃ አወሳሰን ዘዴ ጋር ተያይዞ የፕሮክተር እና የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት የመሳሰሉ የሥራ ዘርፎች እንደገና እንዲጠኑ ለማድረግ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እየሠራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ በዩኒቨርሲቲው ያለውን ሠላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ለማዝለቅ እንዲሁም አጠቃላይ የመማር ማስተማሩን ሂደት በተያዘለት የአካዳሚክ ቀን መቁጠሪያ መሠረት ለማከናወን በቁርጠኝነት ለመሥራት የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት