የታዳሽ ኃይል ቴክኖሎጂ ምርምር ማዕከል ከሳሃይ ሶላር አሶስዬሽን ጋር በመተባበር ከተለያዩ የትምህርት ተቋማት ለተወጣጡ በውሃና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ለሚሠሩ ባለሙያዎች ከጥር 26 - የካቲት 04/2012 ዓ.ም ‹‹Advanced Solar Photovoltaic System›› በሚል ርዕስ የንድፈ ሃሣብና የተግባር ስልጠና ሰጥቷል፡፡፡

ማዕከሉ ይህን ዓለም አቀፋዊ ስልጠና ሲያዘጋጅ ለ4ኛ ጊዜ ሲሆን ከጂንካ፣ አርባ ምንጭ እና ከስዊዘርላንድ ሉትሰርን ዩኒቨርሲቲዎች የተወጣጡ 45 ሰልጣኞች ተሳትፈዋል፡፡ ከአርባ ምንጭና ከስዊዘርላንዱ ሉትሰርን ዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም በዘርፉ ከሚሠሩ የጀርመን ኩባንያዎች የመጡ አሰልጣኞች ስልጠናውን ሰጥተዋል፡፡

የፀሐይ ጨረር መቆጣጠሪያ ምጣድ የፀሐይ ኃይል አሰባሰብ፣ የሚመነጨው የኃይል መጠን የቻርጅ መቆጣጠሪያ ባትሪውን እንዳይጎዳ የኃይል መመጠኛ ቴክኒኮች፣ ባትሪው ሲቃጠልና የአገልግሎት ዘመኑን ሲጨርስ የመለየትና የመቀየር ክሂሎት፣ የፀሐይ ታዳሽ ኃይሉ አጠቃቀም አጠቃላይ ባህርያት፣ የጥገና ዘዴዎችና የፀሐይ ታዳሽ ኃይል መጠቀም ለኢኮኖሚው የሚያበረክተው አስተዋጽኦ በስልጠናው ተዳሰዋል፡፡

ስልጠናው የኤሌክትሪክ ኃይል ባልተዳረሰባቸው የገጠር አካባቢዎች በተለይ ትምህርት ቤቶችና ጤና ጣቢያዎች በፀሐይ ታዳሽ ኃይል የ24 ሰዓት የመብራት አገልግሎት እንዲያገኙ ለማስቻል ያለመ መሆኑን የታዳሽ ኃይል ምርምር ማዕከል ዳይሬክተርና የሳሃይ ሶላር ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ዘላለም ግርማ ተናግረዋል፡፡

ስልጠናው ከዚህ ቀደም በዩኒቨርሲቲው መሠረታዊ የፀሐይ ታዳሽ ኃይል ስልጠና ተብሎ ይሠጥ እንደነበር የገለጹት አቶ ዘላለም ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ ደረጃውን በማሳደግ ‹‹Advanced Solar Photovoltaic System Training›› በሚል እየተሰጠ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡ ሰልጣኞች ያገኙትን እውቀት በተመረጡ 2 የገጠር ትምህርት ቤቶች በማውረድ በተግባር እንዲያሳዩ ተደርጓልም ብለዋል ፡፡

የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሣይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ የኤሌክትሪክ ኃይል ባላገኙ አካባቢዎች የፀሐይ ታዳሽ ኃይል ተጠቃሚ ከማድረግ አኳያ ዩኒቨርሲቲው ውጤታማ ሥራ እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸው በተለይ የጤና ተቋማትና ትምህርት ቤቶች በቀዳሚነት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከፍተኛ ሥራ መሠራቱን ተናግረዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ከዚህ ቀደም በቀድሞው ጋሞ ጎፋ ዞን ውስጥ የሚገኙ 4 የ2ኛ ደረጃ ት/ቤቶችና 26 ጤና ጣቢያዎች በፀሐይ ኃይል የሚሠራ የ24 ሰዓት የታዳሽ ኃይል አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ አስችሏል፡፡ በቀጣይም ዩኒቨርሲቲው በዘርፉ ከሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ጋር በመሆን የኤሌክትሪክ ኃይል ያልተዳረሰባቸው የጋሞ፣ ጎፋ እና ደቡብ ኦሞ ዞን አካባቢዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ በውሃ ኃይል የሚሠሩ የታዳሽ ኃይል ፕሮጀክቶችን ነድፎ እየሠራ ይገኛል፡፡

በስልጠናው ማጠናቀቂያ ስልጠናውን በአግባቡ ስለመከታተላቸው የሚያረጋግጠውን ምዘና ላለፉ ሰልጣኞች የምስክር ወረቀት ተበርክቷል፡፡