የዩኒቨርሲቲው የእንግሊዝኛ ቋንቋና የICT መምህራን በሚሠሩት ‹‹Improving the quality of English teaching trough ICT tools›› የሚል ጥናት መነሻነት ለአርባ ምንጭ፣ አ/ም/ዩ ኮሚዩኒቲ እና ሳውላ 2ኛ ደረጃና መሰናዶ ት/ቤቶች 22 የእንግሊዝኛ ቋንቋ መምህራን እንግሊዝኛ ቋንቋን ከICT ጋር አቀናጅቶ የማስተማር ክሂሎት ማሻሻያ ስልጠና ከጥር 25- 28/2012 ዓ/ም ተሰጥቷል፡፡ የጥናት ቡድኑ ውስጥ የተካተቱ መምህራን እንዲሁም ከየትምህርት ቤቱ የተወጣጡ የቴክኒክ ድጋፍ ሰጪ ባለሙያዎችና የICT መምህራን ስልጠናውን ሰጥተዋል፡፡ ምስሉን ለማየት ከዚህ ይጫኑ

በዩኒቨርስቲው የእንግሊዝኛ ቋንቋ መምህርና የጥናቱ አስተባባሪ ዶ/ር ተስፋዬ ሀብተማርያም እንደገለጹት የስልጠናው ዓላማ የመምህራንን የICT ክሂሎት በማሻሻል የእንግሊዝኛ ቋንቋ የመማር ማስተማር ሂደት ጥራትን ማሳደግ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በክፍል ውስጥ የተወሰነ የእንግሊዝኛ ቋንቋ የማስተማር ሂደት ተማሪዎች ከመማሪያ ክፍላቸው ውጪ እንግሊዝኛ ቋንቋ የሚያገኙበትና የሚያዳብሩበትን ዕድል የማይፈጥር ነው፡፡ በመሆኑም መምህራን የICT መሣሪያዎችን መጠቀም ቢችሉ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የሚያስችል መሆኑ ስለታመነበት ስልጠናው ተዘጋጅቷል ብለዋል፡፡

መምህራኑ በICT እና የእንግሊዝኛ ቋንቋ ማስተማር ረገድ ምን ደረጃ ላይ እንዳሉ በጥናቱ አስቀድሞ መለየቱን የተናገሩት ዶ/ር ተስፋዬ ከስልጠናው በማስከተል ያገኙትን ክሂሎት ከመማሪያ መጽሐፍቱ ጋር በማዋሃድ ማስተማር የሚችሉበትን ንድፍ እንዲያወጡ በማድረግ ውጤቱ የሚገመገም መሆኑን ገልጸዋል፡፡

እንደ ዶ/ር ተስፋዬ ገለጻ መምህራን ተማሪዎቻቸውን ከክፍል ውስጥ ባሻገር በማኅበራዊ ድረ-ገጽ ግሩፖች አግኝተው ትምህርት እንዲሰጧቸውና ግብረ-መልሱን በክፍል ውስጥ ማቅረብ እንዲችሉ ዕድል መፈጠሩ በድምጽ እና በቪዲዮ ምስል የሚደገፉ ትምህርቶች በቀላሉ ለማስተማር ይረዳል፡፡ ከዚህም ባሻገር ተማሪዎች በ ‹E-learning› በመታገዝ ቤታቸው ሆነው የሚማሯቸውን ትምህርቶች በክፍል ውስጥ በጋራ የበለጠ እንዲያዳብሩ ያደርጋል፡፡ በመሆኑም የመማር ማስተማር ሂደቱ በክፍል ውስጥ ብቻ የተገደበ ሳይሆን ከክፍል ውጪም የሚከናወን ይሆናል፡፡

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የእንግሊዝኛ ቋንቋ መምህርና በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የ3ኛ ዲግሪ ትምህርት ላይ የሚገኙት መ/ር ምኅረተአብ አብርሃም በእንግሊዝኛ ቋንቋ ማስተማር ሂደት ICTን መጠቀም የሚያመጣው ለውጥ ላይ ጥናታቸውን እየሠሩ ይገኛል፡፡ በጥናት ሂደቱ የ2ኛ ደረጃ የእንግሊዝኛ ቋንቋ መምህራን ICTን ተጠቅሞ ከማስተማር አኳያ ያላቸውን እውቀት፣ ክሂሎት፣ አመለካከትና ልምድ ለመመዘን ከመሰልጠናቸው በፊት፣ በስልጠናው ወቅትና ከስልጠናው በኋላ መረጃዎችን እንደሚሰበስቡ መ/ር ምኅረተአብ ተናግረዋል፡፡ እስካሁን ባለው ሂደትም ከተሳታፊ መምህራን የተገኘው ግብዓት ቀጣይ ለምንሠራቸው ሥራዎች አቅጣጫ አመላካች ሆኖናል ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ኮሚዩኒቲ መሰናዶ ት/ቤት መምህር የሆኑት ሰልጣኝ ታሪኩ ጎአ የICT መሣሪያዎችንና የተለያዩ ማኅበራዊ ድረ-ገጾችን ተጠቅመን ከተማሪዎቻችን ጋር የማንበብ፣ የማድመጥና ሌሎችም ክሂሎቶችን የምናዳብርበትን እውቀት ከስልጠናው አግኝተናል ብለዋል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት