7ኛው ዓመታዊ ግምገማዊ የምርምር ዓውደ ጥናት ተካሄደ

ዩኒቨርሲቲው 7ኛውን ዓመታዊ ግምገማዊ የምርምር ዓውደ ጥናት የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ ተመራማሪዎች፣ መምህራን፣ የድኅረ-ምረቃ ተማሪዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ከየካቲት 26-27/2012 ዓ/ም አካሂዷል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት ይህንን ይጫኑ

በዓውደ ጥናቱ ‹‹በጋሞ እና ጎፋ ዞኖች የገጠር አካባቢ መደበኛ ያልሆነ የገንዘብ አያያዝ ተግዳሮቶችና አስተዋጽኦ››፣ ‹‹በጋሞ እና ጎፋ ዞኖች የዓሳ ምርት ገበያን ለማሳደግ የእሴት ሰንሰለት ትንተና ሚና››፣ ‹‹በአርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል በጐልማሶች ላይ የHIV ቫይረስ ስርጭት ሽፋን››፣ ‹‹አባያ ሐይቅ አካባቢ የሚገኝ የመሬት ይዘት ለህንፃ ግንባታ ያለው አመቺነት ጥናት››፣ ‹‹መምህራን የሙያ ሥነ-ምግባርን የተረዱበት መንገድና በሙያው ላይ የፈጠረው ጫና›› ‹‹የጊድቾ ህዝብ ታሪክ ከ1520-1995 ዓ/ም››፣ ‹‹በደቡብ ኢትዮጵያ ገላኔ ተፋሰስ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለው ተፅዕኖና የመፍትሄ አቅጣጫ›› እና ‹‹በነጭ ሣር ብሄራዊ ፓርክ የስጋ በል እንስሳት ጥበቃ ሁኔታ ለዱር እንስሳት አስተዳደር የሚኖረው ፋይዳ›› የሚሉ የምርምር ሥራዎች ቀርበዋል፡፡

የምርምር ዳይሬክቶሬት ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ተሾመ ይርጉ ዓውደ ጥናቱ በዋናነት እየተሠሩ የሚገኙ የምርመር ሥራዎችን አፈፃፀምና የጥራት ደረጃ የዘርፉ ባለሙያዎች በተገኙበት ለመመዘን የተዘጋጀ ነው ብለዋል፡፡ ደረጃውን ጠብቀው ብቁ የምርመር ሥራዎችን በዩኒቨርሲቲውና ዓለም አቀፍ ጆርናሎች ላይ ለማሳተም ግምገማዊ ዓውደ ጥናቱ ወሳኝ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ በ2012 ዓ/ም 525 የምርምር ሥራዎች እና 5 ትላልቅ የምርምር ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ አንደሚገኙ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተሩ ገልጸው ከእነዚህም ውስጥ 100 የሚሆኑት በመጀመሪያ ዙር የምርምር ጥሪ የቀረቡ ሲሆን ከቀሪ 430 የምርምር ሥራዎች 30ዎቹ ብቻ በተያዘው የጊዜ ሠሌዳ ተጠናቀዋል ብለዋል፡፡ በመሆኑም ተመራማሪዎች በቀጣይ በተገቢው የጊዜ ሠሌዳ የምርምር ሥራዎችን እንዲያከናውኑ ዶ/ር ተሾመ አሳስበዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው በአዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ መሠረት የምርምር ዩኒቨርሲቲ እንዲሆን በሣይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር መወሰኑን ተከትሎ ዩኒቨርሲቲው ለምርምር ዘርፍ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል ብለዋል፡፡ ለዚህም ማሳያ በዚህ ዓመት በድምሩ 530 የምርምርና የትልልቅ ፕሮጀክት ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ ዓውደ ጥናቱ የማኅበረሰቡን ችግር ለመፍታት የታለሙ የምርምር ሥራዎች ያሉበትን ደረጃ ለመገምገም፣ የዘርፉ ባለሙያዎች ሣይንሳዊና ሥነ-አመክንዮአዊ ሂስ እንዲሰጡበት እና ዓለም አቀፍ የምርምር ይዘትን የሚያሟሉ ምርምሮች በዩኒቨርሲቲውና ዓለም አቀፍ ጆርናሎች ላይ እንዲታተሙ ለማብቃት የጎላ ሚና አለው ብለዋል፡፡

ተመራማሪዎች በበኩላቸው ግምገማው በምርምር ሂደት ላይ የታዩ ክፍተቶችን በመለየት መስተካከል ያለባቸው ነጥቦች ላይ ከዘርፉ ባለሙያዎች ጋራ የጋራ ምክክር በማድረጋቸው ለወደፊት ሥራቸው እጅግ ጠቃሚ ነው ብለዋል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዪኒኬሽን ዳይሬክቶሬት