ዩኒቨርሲቲው በጋሞ ዞን ጋጮ ባባና በአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳዎች በተከሰተው የመሬት ናዳና የጎርፍ አደጋ ምክንያት ለተፈናቀሉ ወገኖች ጥር 29/2012 ዓ/ም 150 ኩንታል በቆሎ ድጋፍ አድርጓል፡፡

በጋጮ ባባ ወረዳ በጋፄ ቀበሌ ልዩ ስሙ ሻሮ ንዑስ ቀበሌ ጥር 21/2012 ዓ/ም በጣለው ከባድ ዝናብ ናዳ ተከስቶ የ4 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ 726 የቤተሰብ አባላት ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል፡፡ በተመሳሳይ በአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ጥር 26/2012 ዓ/ም በጣለው ከፍተኛ ዝናብ የሰጎ እና የሲሌ ወንዞች በመሙላታቸው በተከሰተው የጎርፍ አደጋ በቆላ ሸሌ፣ ሸሌ ሜላ እና ኤልጎ ቀበሌያት በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል፡፡ ምስሉን ለማየት

የጋጮ ባባ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ደረሰ ዳይሾሌ ዩኒቨርሲቲው ላበረከተው ድጋፍ በተጎጂ ቤተሰቦችና በወረዳው ስም ምስጋና አቅርበው በአደጋው የተጎዱ ወገኖችን በዘላቂነት ለማቋቋም አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ዩኒቨርሲቲው ከወረዳው ጎን እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በአደጋው የተጎዱና ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን በዘላቂነት ለማቋቋም አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዩኒቨርሲቲው ዝግጁ ነው ብለዋል፡፡

የማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በበኩላቸው ለተከሰተው አደጋ አፋጣኝ ምላሽ መስጠት ስለሚያስፈልግ ዩኒቨርሲቲው የመጀመሪያ ዙር ለዕለት ደራሽ የሚሆን የምግብ እህል ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡ ጎርፉን ተከትሎ ሊከሰት የሚችለውን ውሃ ወለድ በሽታ ለመከላከል ዩኒቨርሲቲው የጤና ባለሙያዎችን በአካባቢው በማሰማራት የመከላከል ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል፡፡ በቀጣይም ከዞን፣ ከወረዳና ከቀበሌያት ከተወጣጡ ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በጥናትና ምርምር የተደገፈ የተፋሰስ ሥራ እንዲሁም ለኅብረተሰቡ ግንዛቤ በመፍጠር ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት ዩኒቨርሲቲው ይሠራል ብለዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ የተመራ የልዑካን ቡድን በጋጮ ባባ ወረዳ እንዲሁም በአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር የቻለ ከበደ የተመራ የልዑካን ቡድን በአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ በመገኘት የደረሰውን ጉዳት ተመልክቷል፡፡