ዩኒቨርሲቲው ፈረንሳይ አገር ከሚገኘው CIMPA የተሰኘ ማዕከል ጋር የጀመረው ግንኙነት ተጠናክሮ ቀጥሏል

ዩኒቨርሲቲው የሒሳብ ትምህርትና ምርምርን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስፋፋትና ለማሳደግ ከሚሠራውና ፈረንሳይ አገር ከሚገኘው ‹‹International Center for Pure and Applied Mathematics›› CIMPA ማዕከል ጋር የጀመረው ግንኙነት ተጠናከሮ መቀጠሉ ተገለጸ፡፡ ዩኒቨርሲቲው በ2021 ‹‹CIMPA School›› ተብሎ የሚጠራውን ዓለም አቀፍ የምርምር ኮንፍረንስ እንዲያዘጋጅም ተመርጧል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት ይህንን ይጫኑ

የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር የቻለ ከበደ እንደገለጹት ከማዕከሉ የመጡ ታዋቂ ፕሮፌሰሮች ለተማሪዎቻችን ኮርሶችን እንዲሁም ለመምህራን የተለያዩ ስልጠናዎችን በመስጠት ትልቅ አስተዋጽኦ ሲያበረክቱ እንደነበር አስታውሰው ዘንድሮም ይህ ተግባር ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል፡፡ የትምህርት አሰጣጣችን ዓለም አቀፍ ደረጃውንና ጥራቱን የጠበቀ እንዲሆን ለማድረግ ከመሰል ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር የሚደረጉ ሥራዎች ሚናቸው የጎላ በመሆኑ ሥራው ለሌሎች ትምህርት ክፍሎችም በሞዴልነት የሚወሰድ መሆኑን ዶ/ር የቻለ ተናግረዋል፡፡

CIMPA በሥሩ በርካታ የመስኩን ምሁራን የያዘ ዓለም አቀፍ ማዕከል መሆኑን የገለፁት ዶ/ር የቻለ በቅርቡ የማዕከሉ የምስራቅ አፍሪካ ቅርንጫፍ በዩኒቨርሲቲያችን ይከፈታል ብለዋል፡፡

የCIMPA ኤክስክዩቲቭ ዳይሬክተር ፕሮፌሰር Ludovic Rifford እንዳሉት ከዩኒቨርሲቲው ጋር የተጀመረው ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ሲሆን በ2011 ዓ/ም በተፈራረሙት የመግባቢያ ስምምነት መሠረት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው፡፡ በቀጣይ ከፈረንሳይ ኤምባሲ ጋር ተነጋግረን ከአርባ ምንጭና ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመሆን ሳንድዊች የ2ኛ እና 3ኛ ዲግሪ ፕሮግራሞችን ለመክፈት እየሠራን ነው ብለዋል፡፡ እ.ኤ.አ በ2021 በርካታ የመስኩ ምሁራን የሚሳተፉበት ዓለም አቀፍ የምርምር ኮንፍረንስ እንዲያዘጋጅ ዩኒቨርሲቲው መመረጡ ዩኒቨርሲቲውን በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሚያደርግና በሌሎችም ዘርፎች የሚጠቅም መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የተፈጥሮ ሣይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ፈቃዱ ማሴቦ እንደገለጹት የሒሳብ ትምህርት ክፍል ከዓለም አቀፉ ማዕከል ጋር ግንኙነት በመጀመር ዩኒቨርሲቲው ዓለም አቀፍ ዕይታ ውስጥ እንዲገባ እንዲሁም ተማሪዎቻችን ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት እንዲያገኙ ማድረጉ ሊበረታታ የሚገባውና አርአያ የሚሆን ነው ብለዋል፡፡ አሁን ከዩኒቨርሲቲያችን ተማሪዎች አልፎ ከሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ጭምር የመጡ ተማሪዎች ኮርሶችን እየወሰዱ መሆኑን የገለፁት ዲኑ ይህም ከማዕከሉ ጋር የተጀመረው ግንኙነት እየሰፋ መምጣቱን ያመላክታል ብለዋል፡፡

የሒሳብ ትምህርት ክፍል ኃላፊ ዶ/ር ስምዖን ደርኬ በበኩላቸው በ2011 ዓ/ም ከCIMPA ጋር በተጀመረው ግንኙነት ከመላው ዓለም የተወጣጡ 8 ፕሮፌሰሮች መጥተው ለዩኒቨርሲቲው የ3ኛ ዲግሪ ተማሪዎች ኮርሶችን እንደሰጡና ሰሚናሮችን እንዳዘጋጁ አስታውሰው በ2012 ዓ/ም 9 ፕሮፌሰሮች የሚመጡ ሲሆን እስካሁን ባለው ሂደት የማዕከሉን ኤክስክዩቲቭ ዳይሬክተር ጨምሮ 3 ፕሮፌሰሮች መጥተው ኮርሶችን የመስጠትና ሴሚናሮችን የማዘጋጀት ሥራ አከናውነዋል ብለዋል፡፡

በትምህርት ክፍሉ ለ3ኛ ዲግሪ ተማሪዎች የምርምር አማካሪ ማግኘት ትልቅ ችግር ሆኖ እንደቆየ የተናገሩት ዶ/ር ስምዖን ግንኙነቱ ከተፈጠረ በኋላ ተማሪዎቻችን ከማዕከሉ አማካሪዎችን እያገኙ ነው ብለዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ከCIMPA ጋር በጋራ ለመሥራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ሚያዝያ 2/2011 ዓ/ም መፈራረሙ ይታወሳል፡፡