የጫሞ ካምፓስ የ2012 ዓ/ም የ1ኛ ወሰነ ትምህርት መማር ማስተማር ሥራ በስኬት መጠናቀቁ ተገለጸ

በማኅበራዊ ሣይንስና ስነ- ሰብ ኮሌጅ እና በቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ እንዲሁም በህግ እና በስነ-ትምህርትና ስነ-ባህርይ ሣይንስ ት/ቤቶች የ2012 ዓ/ም 1ኛ ወሰነ ትምህርት በስኬት መጠናቀቁን የኮሌጆቹና የት/ቤቶቹ ዲኖች ገልጸዋል፡፡

የማኅበራዊ ሣይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ ዲን እና የካምፓሱ አስተባባሪ ዶ/ር ሙሉጌታ ደበሌ እንደገለጹት የ1ኛ ወሰነ ትምህርት የመማር ማስተማር ሂደት እጅግ በተሳካና በሰላማዊ መንገድ ተጠናቋል ብለዋል፡፡ በጥናትና ምርምር አተገባበር ላይ ለመምህራን ስልጠናዎችን በመስጠት ወደ ሥራ እንዲገቡ በመደረጉ በተለይም ነባር መምህራን በተቀላጠፈ ሁኔታ ምርምር እያከናወኑ እንደሚገኙም ጠቁመዋል፡፡

ከመጀመሪያ ቀን የመጀመሪያ ክፍለ ጊዜ ጀምሮ የመማር ማስተማር ሂደቱ ያለምንም መስተጓጎል በተሻለና በሰላማዊ ሁኔታ መፈፀሙን የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ዲን አቶ ጌታሰው ያረጋል ገልጸዋል፡፡ መምህራን ከተለያዩ ኢንደስትሪዎች ልምድ እንዲቀስሙና ተማሪዎች በክፍል ውስጥ የተማሩትን በተግባር በኢንደስትሪዎች እንዲያዩ ተደርጓልም ብለዋል፡፡ በተጨማሪም በጥናትና ምርምር ዙሪያ ያሉ ክፍተቶችን በመቅረፍ መምህራን ወደ ትግበራ እንዲገቡ ለማስቻል የተለያዩ የአቅም ማጎልበቻ ስልጠናዎችን በመስጠት በርካታ መምህራን በጥናትና ምርምር ሥራዎች ላይ መሰማራታቸውን ዲኑ ተናግረዋል፡፡

የህግ ትምህርት ቤት ዲን አቶ ደርሶልኝ የኔአባት በበኩላቸው የመማር ማስተማር ሥራዎችን ለማፋጠንና ውጤታማ ለማድረግ ብሎም ጥራቱን ለማስጠበቅ መምህራንን የክፍል ተጠሪ አድርጎ ከመመደብ ጀምሮ የክረምትና የማታ የማስተርስ ፕሮግራም ሥርዓተ-ትምህርት ክለሳ እንዲሁም ቀደም ሲል በተለያዩ ምክንያቶች የድጋሚ የመውጫ ፈተናን ያላለፉ ተማሪዎች በድጋሚ ፈተናውን በአግባቡ እንዲወስዱ ተደርጓል፡፡ በተጨማሪም የ5ኛ ዓመት ተማሪዎች ለመውጫ ፈተና ዝግጅት በቂ ጊዜ እንዲኖራቸው ለማስቻል በ1ኛ ወሰነ ትምርት የመመረቂያ ጽሑፋቸውን እንዲሠሩና እንዲያስተቹ ተደርጓል ብለዋል፡፡ ከጠቅላይ ፍርድ ቤት የተገኙ አዳዲስ መጽሐፍት እና የተጓደሉ ግብዓቶች ተባዝተው ወደ ቤተ-መጽሐፍት የገቡ ሲሆን በተከታታይ ምዘና ረገድ ለመምህራን ኦረንቴሽን በመስጠትና ሂደቱን አስመልክቶ ከተማሪዎች ጋር ውይይት በማድረግ ጉድለቶችን ለማስተካከል ሰፊ ሥራዎች መሠራታቸውን አቶ ደርሶልኝ ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይም የስነ-ትምህርትና ስነ-ባህርይ ሣይንስ ትምህርት ቤት ዲን አቶ አንለይ ብርሃኑ እንደተናገሩት ተከታታይ ምዘናዎች፣ ቴስቶችና አሳይመንቶች በተገቢው መንገድ እንዲከናወኑ በትምህርት ክፍል ኃላፊዎች አማካይነት ክትትልና ቁጥጥር ተደርጎ ኮርሶች የተጠናቀቁ ሲሆን የተማሪዎች ውጤት ላይም መምህራን በወቅቱ ግብረ መልስ እንዲሰጡ ተደርጓል፡፡ በተጨማሪም አዲስ ለተቀጠሩ መምህራን መሠረታዊ የማስተማር ክሂሎት እና ለሴት ተማሪዎች የህይወት ክሂሎት ስልጠና የተሰጠ ሲሆን ለሁሉም የ1ኛ ዓመት ተማሪዎች የእንግሊዝኛ ቋንቋ ችሎታቸው ምን ደረጃ ላይ እንዳለ የቅድመ መለኪያ ፈተና በመስጠት ከ50 በታች ላመጡ ተማሪዎች ለ8 ሣምንታት የቆየ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ማሻሻያ እና ሌሎች የመማር ማስተማር ሂደትን ውጤታማ ሊያደርጉ የሚችሉ ሥራዎች መሠራታቸውን አቶ አንለይ ጠቁመዋል፡፡

ለ1ኛ ዓመት ተማሪዎች በምክንያት የማሰብ፣ የመመራመር፣ የመጠየቅ እና በራስ የመተማመን አጠቃላይ ዕውቀት የሚያስጨብጡ ኮመን ኮርሶች የተሰጡ ሲሆን ኮርሶቹ በቁጥር በርካታ በመሆናቸው በተማሪዎች ዘንድ አለመረጋጋትን ያስከተሉ ነበሩ፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ ከፍተኛ ልምድ ያላቸውና ትምህርቱን አቅልለው ሊያቀርቡላቸው የሚችሉ መምህራንና በካምፓሱ ያሉ ዲኖች በሴክሽን ተጠሪነት ተመድበው ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡ ይህም ተማሪዎቹ ተረጋግተው ትምርታቸውን እንዲማሩና ሃሳባቸውን ያለምንም ስጋትና ፍርሃት እንዲያንሸራሽሩ ረድቷቸዋል፡፡ ሂደቱ የሣይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ባወጣው መመሪያ መሠረት የተተገበረ ሲሆን እጅግ ፍትሃዊና አተገባበሩና ይዘቱ ሙሉ በሙሉ ወጥነት ያለው ነው፡፡ የሚሰጡት ኮርሶች በቀጣይ ለሚመርጡት የትምህርት መስክ ከፍተኛ እገዛ የሚያደርጉ ሲሆን በ2ኛ ወሰነ ትምህርት በሚሰጡ ኮርሶች ላይ በተፈጥሮ እና በማኅበራዊ ሣይንስ ተማሪዎች መካከል የተወሰኑ ኮርሶች ልየታ ይኖራል፡፡

በካምፓሱ የማኅበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ በልማትና በምዕራብ አባያ ት/ቤት ከ1ኛ-4ኛ ክፍል ላሉ 150 ተማሪዎች የእንግሊዝኛ ቋንቋ የንግግር ክሂሎት ማሻሻያ ትምህርት ለመስጠት ቅድመ ሁኔታዎች የተጠናቀቁ ሲሆን በመሠረታዊ የሂሳብ አያያዝ ዘዴለ መምህራን የሶፍትዌር ስልጠና መስጠት እንዲሁም የቢዝነስ ሥራዎችን ሊያግዙ የሚችሉ የዳሰሳ ጥናቶች ተካሂደዋል፡፡

በነፃ የህግ ድጋፍ አገልግሎት በ7 ማዕከላት እስከ ሰበር ችሎት ቆሞ የመከራከር፣ የማማከርና ሰነድ የማዘጋጀት እንዲሁም በሁሉም ፍርድ ቤቶች ችሎት ከመጀመሩ በፊት በነፃ የህግ ድጋፍ ባለሙያዎች አማካይነት ትምህርት የመስጠት ሥራዎችም ተሠርተዋል፡፡ ‹‹የህግ መንገድ›› የተሰኘ የሬዲዮ ፕሮግራም ተዘጋጅቶ እየቀረበም ይገኛል፡፡

በተጨማሪም ለርዕሳነ መምህራን፣ ለሱፐርቫይዘሮች፣ ለወረዳ ጽ/ቤት ኃላፊዎች፣ ለቅድመ መደበኛ መምህራን እና ለልዩ ፍላጎትና የአካቶ ትምህርት ባለሙያዎች፣ ከተማሪዎች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ላላቸው የዩኒቨርሲቲው ሠራተኞችና ለመምህራን የተግባቦት ክሂሎት ማሻሻያ፣ የማማከር አገልግሎት፣ የከፍተኛ ዲፕሎማና ሌሎች የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች ለዘርፎቹ እንደየአስፈላጊነታቸው ተለይተው ተሰጥተዋል፡፡

የመማር ማስተማሩ ሥራ ያለምንም መቆራረጥ በሰላማዊ መንገድ መከናወኑ፣ መምህራን ለምርምር ያላቸው ፍላጎት እየተጠናከረ መምጣቱ፣ ከዓለም ዓቀፍ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ያለው ግንኙነት እየተጠናከረ መሆኑ እና የ1ኛ ዓመት ተማሪዎች በቀጣይ የዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ሊያጋጥሟቸው ስለሚችሉ ጉዳዮች በቂ መረጃ እንዲያገኙ መደረጉ በግማሽ ዓመቱ አፈፃፀም የሚጠቀሱ ጠንካራ ጎኖች ናቸው፡፡

የቤተ-ሙከራ አለመደራጀት፣ የምርምር ተግባራት በተወሰኑ አካባቢዎች ላይ ብቻ መወሰን፣ የመምህራን ፍልሰት፣ የግዢ መጓተት፣ የበጀትና የግብዓት እጥረት፣ የተጀመሩ የምርምር ፕሮጀክቶች በታቀደው መሠረት አለመጠናቀቅ፣ የመማሪያ ክፍሎች፣ ቢሮዎችና የተማሪዎች ማደሪያ እጥረት እንዲሁም በጋራ ኮርስ አስተባባሪዎች ላይ ከፍተኛ ጫና መኖሩ በግማሽ ዓመቱ በዋናነት ያጋጠሙ ተግዳሮቶች መሆናቸውን የካምፓሱ ዲኖች ጠቁመዋል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት