አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በሳሃይ ሶላር ፕሮጀክት ጉልታ ሙሉ 1ኛ ደረጃ ት/ቤትን የ24 ሰዓት የፀሐይ ታዳሽ ኃይል ተጠቃሚ አደረገ

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በሳሀይ ሶላር ፕሮጀክት አማካይነት በጨንቻ ወረዳ የሚገኘውን ጉልታ ሙሉ 1ኛ ደረጃ ት/ቤት ከየካቲት 20/2012 ዓ/ም ጀምሮ የ24 ሰዓት የፀሐይ ታዳሽ ኃይል ተጠቃሚ አድርጓል፡፡

የጉልታ ሙሉ 1ኛ ደረጃ ት/ቤት ር/መ/ር አቶ አብርሃም ዓባይ ት/ቤቱ በ1942 ዓ/ም የተመሠረተ መሆኑን ተናግረው አሁን ት/ቤቱ ያለበት ደረጃ ከዕድሜው አንፃር ሲመዘን ዕድገቱ ዝቅተኛ ነው ብለዋል፡፡ ት/ቤቱ ከዚህ ቀደም ከሌላ ተቋም 15 ኮምፐዩተሮችንና 2 ኮፒ ማሽኖችን በድጋፍ አግኝቶ የነበረ ቢሆንም በአካባቢው የኤሌክትሪክ አገልግሎት ባለመኖሩ ዕቃዎቹን መጠቀም እንዳልተቻለም ጠቁመዋል፡፡ አሁን ላይ ዩኒቨርሲቲው የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ስላደረጋቸው ማሽኖቹን መጠቀም እንደሚጀምሩ ተናግረው ዩኒቨርሲቲው ላደረገው ድጋፍ ልባዊ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

የጉልታ ቀበሌ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘነበ ንጋቱ ዩኒቨርሲቲው ያደረገው ድጋፍ የተሻሉ ተማሪዎችን ለማፍራት እንደሚያግዝ ገልጸው ዩኒቨርሲቲው የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡

የአካባቢው ማኅበረሰብና የአገር ሽማግሌዎች በሰጡት አስተያየት ድጋፉ ትውልዱ ጥሩ ተስፋ እንዲያይ ያደረገ መሆኑን ጠቅሰው ያልተማሩና ደሃ አባቶቻችን የመሠረቱት ት/ቤት ለትውልድ እንዲተላለፍና ለታሪክ እንዲቀመጥ የመንግሥት ትኩረትና የዩኒቨርሲቲው ክትትል እንዳይለየን ብለዋል፡፡

ሳሃይ ሶላር ፕሮጀክት በዋናነት የኤሌክትሪክ ኃይል ባልተዳረሰባቸው የገጠር አካባቢዎች በተለይ ትምህርት ቤቶችንና ጤና ጣቢያዎችን በፀሐይ ታዳሽ ኃይል የ24 ሰዓት የመብራት አገልግሎት እንዲያገኙ ለማስቻል የሚሠራ መሆኑን በዩኒቨርሲቲው የታዳሽ ኃይል ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር አቶ ዘላለም ግርማ ጠቁመዋል፡፡

ፕሮጀክቱ እ.ኤ.አ ሚያዝያ/2015 ዓ/ም ሥራውን የጀመረ ሲሆን በእስከ አሁን ቆይታውም በጋሞና ጎፋ ዞኖች የሚገኙ 14 ትምህርት ቤቶችንና 26 ጤና ጣቢያዎችን የ24 ሰዓት የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲያገኙ አስችሏል፡፡ በተጨማሪም ት/ቤቶችና የጤና ተቋማት ለሬዲዮ፣ ቴሌቪዥን፣ ኮምፕዩተር፣ ማባዣ ማሽኖች፣ ላቦራቶሪ፣ ማቀዝቀዣ የሚሆን ኃይልና የ24 ሰዓት የመብራት አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርጓል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት