በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ስርጭት ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተቋቋመው ግብረ-ኃይል ማኅበረሰብ የማንቃት ቅስቀሳ እያካሄደ ነው

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ስርጭት ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተቋቋመው ግብረ-ኃይል ንዑስ ግብረ-ኃይል አባል የሆኑ የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የጤና ባለሙያዎች በአርባ ምንጭ ከተማ እንዲሁም በአርባ ምንጭ ዙሪያ፣ ጨንቻ፣ ካምባ፣ ገረሴና ቆጎታ ወረዳዎች በመገኘት በኮሮና ቫይረስ መከላከያ፣ መተላለፊያና ሊደረጉ በሚገባቸው ጥንቃቄዎች ዙሪያ ለአካባባቢው ማኅበረሰብ፣ የጤና ባለሙያዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ አከናውነዋል፡፡

ግብረ-ኃይሉ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ እና በክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺይፍ ኤክስክዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ታምሩ ሽብሩ አማካኝነት በሲቀላ ገበያ በኮሮና ወረርሽኝ መከላከል ዙሪያ መጋቢት 25/2012 ዓ/ም የግንዛቤ ማስጨበጫ መልዕክት እንዲተላለፍ አድርጓል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት ይህንን ይጫኑ

ዶ/ር ዳምጠው ባስተላለፉት መልዕክት የኮሮና ቫይረስ ዓለም አቀፍ ወረርሽኝና የዓለማችን ኃያላን ሀገራት ጭምር እየተፈታተነ ያለ በሽታ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡ በሽታው በሀገራችን ከተከሰተ ጊዜ አንስቶ መንግሥት ወረርሽኙን ለመከላከል ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ የጠቆሙት ዶ/ር ዳምጠው ሕዝቡ ከጤና ባለሙያዎችና ከመንግሥት አካላት የሚተላለፉ መመሪያዎችንና መልዕክቶችን ተግባራዊ ማድረግ አለበት ብለዋል፡፡

በተመሳሳሳይም የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺይፍ ኤክስክዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ታምሩ ሽብሩ በበኩላቸው የኮሮና ቫይረስ ገዳይ፣ የመተንፈሻ አካላትን የሚያጠቃና በቀላሉ የማይድን በሽታ መሆኑን አስገንዝበው ኅብረተሰቡ በዋናናት የግል ንጽህናና ማኅበራዊ ርቀትን በመጠበቅ፣ እጅን አዘውትሮ በሳሙናና በውኃ በደንብ በመታጠብ፣ ንኪኪን ሙሉ በሙሉ በማቆም፣ ባለመጨባበጥ፣ ባለመሰብሰብና ከቤት ውጭ የሚደረጉ እንቅሰቃሴዎችን በመገደብ እንዲሁም ሌሎች የመከላከያ መንገዶችን የጤና ባለሙያዎች በተጨማሪ በሚሰጡት መመሪያ መሠረት ራሱን ከዚህ ገዳይ በሽታ መጠበቅ አለበት ሲሉ አጽንዖት ሰጥተው አሳስበዋል፡፡

ጫኖ ሚሌ፣ ሻራ፣ ጫኖ ዶርጋ፣ ጨንቻ ከተማ፣ ዶርዜ፣ ኤዞ፣ ቆላ ሼሌ፣ ሼሌ ሜላ፣ ሲሌ ሲራ፣ ባልታ፣ ገረሴ ደንብሌ እንዲሁም በአርባ ምንጭ ከተማ በሚገኙ ሁሉም ክ/ከተሞች እስካሁን ማኅበረሰቡን የማስተማርና የማንቃት ተግባራት ከተከናወነባቸው አካባቢዎች መካከል ይገኙበታል፡፡ግብረ-ኃይሉ በቀጣይም የጀመረውን ማኅበረሰብ የማንቃት ሥራ በሌሎች አካባቢዎችም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጿል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት